ካጣሁሽ በኋላ /የግጥም ጥግ/

0

ካጣሁሽ በኋላ….
ያላንቺ እንደማልኖር ፣ ለሀገር ተናግሬ
ከሰማይ ጠቀስ ፎቅ ፣ እራሴን ወርውሬ
እራሴን ለመግደል ፣ ቀረሁ ተመኝቼ
ለሞት የሚያበቃ…
ሰማይ ጠቀስ ህንፃ ፣ ባገሩ አጥቼ፡፡
እናም እልሻለሁ…
በሀገራችን ያሉ ፣
ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ፣ ከምድር ቢርቁም
ራሴን ብወረውር …
ለመሰበሪያ እንጂ ፣ ለሞት አያበቁም፡፡
ደግሞ ተሰብሬ…
እኔን ለማስታመም ፣ ሌላው ከሚቸገር
ልኑር ብዬ እንጂ….
ለመሞት ያሰብሁት፣ ያጣሁሽ ቀን ነበር፡፡
…………………………………..
ካጣሁሽ በኋላ….
ታንቄ ለመሞት፣
ስጋዬና ነፍሴ፣
ከዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ፣ ሳለ ተንጠልጥሎ
ትዝታሽ ቢከብደው…
የዛፉ ቅርንጫፍ ፣ ጣለኝ ተገንጥሎ
መርዝም ጠጥቻለሁ…
ያጋሳኛል እንጂ ፣ ፍቅር አይሞትም ብሎ፡፡
እናም እልሻለሁ….
ዛፍ ባየሁኝ ቁጥር ፣
የመገንጠል ሀሳብ ፣ ደርሶ ትዝ ይለኛል
ከዛን ቀን ጀምሮ…..
መርዝ አልገል ያለው ፣
መርዝ የሆነ ኑሮ ፣ ፍቅር ይመስለኛል፡፡
………………………………..
ካጣሁሽ በኋላ……
መኪና ጎማ ውስጥ፣
ገብቼ ለመሞት ፣ ሀሳቡ ነበረኝ
ቅድሚያ ለእግረኛ፣
ባለመስጠት ምክንያት፣
የሚታሰር ሾፌር ፣ ሕይወት አሳዘነኝ፡፡
መንገድ ለጠፋበት ፣ መንገዱን ለሳተ
መኪና መንገድ ላይ ፣ ተገጭቶ ለሞተ
ለእግረኛ ሕይወት ፣ ሾፌር ከሚታሰር
ልኑር ብዬ እንጂ….
ለመሞት ያሰብሁት ፣ ያጣሁሽ ቀን ነበር፡፡
………………………………….
ካጣሁሽ በኋላ…..
‹‹ወንዝ ውስጥ ገብተ ሙት››፣
የሚል መካሪ ሀሳብ ፣ ውስጤ ተከሰተ
የምሞትበትን
ወንዝ እየፈለግሁኝ….
መካሪ ሃሳቤ ፣ውሃ ጠምቶት ሞተ፡፡
እናም እልሻለሁ….
ወንዞቻችን ሁሉ ስለተገደቡ፣
የመሞቻዬን ወንዝ ፣ ማግኘት ተስኖኛል
‹‹ልፋ›› ቢለኝ እንጂ…
ውሃ በሌለበት፣
ውሃ ወስዶኝ መሞት ፣ እንዴት ይቻለኛል፡፡
………………………………..
ካጣሁሽ በኋላ……
በሞቴ እንድረሳሽ ፣ኖሬ እንዳልከፋ
ይገደለኛል ብዬ….
ኮረንቲ ብጨብጥ ፣ ወዲያው መብራት ጠፋ፡፡
እስካሁን አልመጣም ፣ እንደጠፋ ቀረ
እንዴት ጨለማ ውስጥ….
መሞት ይቻለዋል ፣ ብርሃን ያፈቀረ
……………………………
ብቻ ምን አለፋሽ…..
ካጣሁሽ በኋላ፣
ኮረንቲ ስጨብጥ ፣ መብራት የሚያጠፉ
መኪና ጎማ ውስጥ….
ገብቼ እንዳልሞት ፣ ሾፌር የሚያስከፉ
ወንዙን ገድበውት ….
መካሪ ሀሳቤን በጥም የሚገድሉ
ተፈጥፍጬ እንዳልሞት….
ሰማይ ጠቀስ ህንፃን ፣ መገንባት ያልቻሉ
ትዝታን መሸከም….
የማይችሉን ዛፎች በደቦ ሚተክሉ
አካላቶች ሁሉ
ምነው ልክ እንደኔ…
ሚወዱትን አጥተው፣
መሞቻ ቦታ አጥተው ፣ መከራ በበሉ፡፡
በማለት አምርሬ
ከፉ ሥራቸውን…
አደባባይ መሃል ፣ ጮኼ ተናግሬ
ይገድሉኛል ብዬ እየተጠባበቅሁ….
ባሸባሪነት ስም ፣ አለሁ ተጠርጥሬ፡፡
………………………….
ብቻ ምን አለፋሽ…..
ይገድለኛል ብዬ፣
የሞከርሁት ሁሉ ፣ አልሆነም ዓለሜ
እስከሚሆን ድረስ ፣ በአንዲት ኪሎ አቅሜ
ኩንታል ትዝታሽን ፣ አለሁ ተሸክሜ፡፡
አለሁ!!!!!

source : facebook