በርካታ የኦሮሚያ ስፍራዎች ወደ ሶማሌ ክልል መጠቃለላቸውን የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት በግልጽ ተናገሩ

0

በጭናክሰንና በባቢሌ ከፍተኛ ውጥረትና ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች ትጥቅ እንዲፈቱ ተደርጓል።

በኦሮሚያና በሶማሊያ ድንበር አካባቢዎች ይፈጠሩ የነበሩ ግጭቶች እልባት እንዳገኙ በቅርቡ በመንግስት መገናኛ ብዙሀን በተደጋጋሚ ቢገለጽም ሁኔታው ወደ አደገኛ መንገድ እያመራ እንደሆነ የባቢሌና የጭናክሰን ነዋሪዎች በተለይ ለኢሳት ገልጸዋል።

የሶማሌው ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሀመድ እሁድ ዕለት በመከላከያ ሰራዊትና በራሳቸው ፈጥኖ ደራጽ ጦር ታጅበው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ወደሚገኙት የጭናክሰን አካባቢዎች መምጣታቸውን የሚናገሩት የወረዳው ነዋሪዎች አቶ አብዲ በሥፍራው እንደደረሱ የምሥራቅ ሀረርጌ ፖሊሶች ትጥቃቸውን እንዲፈቱና ከመከላከያ ጋር ሆነው በዱላ ብቻ እንዲጠብቁ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

Related image
አስቀድሞ መከላከያ ወደ አካባቢው ከገባና ሕዝቡ ከተከበበ በኋላ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ሊያናግራችሁ ስለሆነ ውጡ ተብለው እንዲወጡ መደረጋቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ ሕዝቡ ከተሰበሰበ በኋላ ግን የሶማሌ ክልሉ ፕሬዚዳንት ታጅበው በመምጣት እስከዛሬ በኦሮሚያ ክልል ስር የነበሩትን ቀበሌዎቻችንን በሶማሌ ክልል ስር እንዲሆኑ መወሰናቸውን በግልጽ ነግረውናል ብለዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ከጭናክሰን ወረዳ ብቻ 15 የኦሮሚያ ቀበሌዎች ለሶማሌ ክልል እንደተወሰኑ አቶ አብዱ ተናግረዋል። 15ቱ ወረዳዎችም አንባሮ አንድ አንባሮ ሁለት ኦርዳፋ አንድ፣ኦርዳፋ ሁለት፣ ኦርዳፋ ሦስት፣ ቢዮ ጋባብዱ፣ ኡሳሌ፣ ኡስወይኒ፣ ማካኒሳ ኦሮሞ፣ ገላ፣አርባጅድ፣ቱራኖድ፣ኮሮሊ ካባ፣ሀሰን ኤቦ እና ካልማሌ ናቸው። ውሳኔው እጅግ ለም የሆነውን የጭናክሰንን መሬት ከኦሮሚያ ክልል ለማውጣት የተደረገ ሴራ ነው ሲሉም ነዋሪዎቹ ቁጣቸውን ገልጸዋል። በአቶ አብዱ ንግግር አብዛኛው ሕዝብ ግራ በመጋባቱ ስብሰባውን እያቋረጠ መሄዱንና ረብሻና የተቃውሞ ድምጽ መሰማቱንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

በዚህ ሁኔታ ህዝቡ ብስጭቱን እየገለጸበት ባለበት ወቅት ይባስ ብሎ በዛሬው ዕለት አቶ አብዲ ልክ እንደጭናክሰኙ ሁሉ በመከላከያና በልዩ ኃይላቸው ታጅበው ከሀረር 42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘውና የኦሮሚያ ክልል ይዞታ ወደሆኑ የባቢሌ ግዛቶች በመሄድ ቦታዎቹ ወደ ሶማሌ እንዲካለሉ ውሳኔ መተላለፉን ህዝቡን ሰብስበው ተናግረዋል። በዚህን ጊዜ ህዝቡ በብስጭት እንዳለ ስብሰባውን ጥሎ የወጣ ሲሆን፣ በገንዘብና በጫት የተደለሉ የአካባቢው መስተዳድር አካላት የተቆጣውን ሕዝብ ለማባብነል ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል።

ይህን የኦሮሚያ ክልል ይዞታዎች የሆኑ ቦታዎችን በሶማሌ ክልል ለማካለል እየተደረገ ባለው ከላይ ጀምሮ የታቀደ ዘመቻ ከመንግስትና ከታዋቂዋ የጫት ነጋዴ ከወይዘሮ ሱራ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር መመደቡን የጠቀሱት የመስተዳድር ምንጮች ገንዘቡ በማካለሉ ሂደት ተቃውሞ ለሚያሰሙና ለሚያንገራግሩ ከዞን ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ላሉ ወጣቶች መደለያ የሚውል ነው ብለዋል።
ይህ ሁሉ በሚሆንበትና የሶማሌ ክልሉ ፕሬዚዳንት ኦሮሚያ ክልል እንዳሻቸው እየገቡ ሕዝቡን በመከላከያ አስገድደው ወደ ሶማሌ ክልል ተጠቃላችኋል ሲሉ ከአቶ ለማ መገርሳ ጀምሮ የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት አንድም ነገር አለመተንፈሳቸው እጅግ እንደገረማቸውና እንዳሳዘናቸው ነዋሪዎቹ በቁጭት ተናግረዋል።

ይህ የሆነውም ሆነ ተብሎ ከላይ ጀምሮ የተቀነባበረ ሴራ ስላለ እንደሆነ ተረድተናል ያሉት ነዋሪዎቹ ያለ ፍላጎታችን ያለምንም ህጋዊና ታሪካዊ መሰረት የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ናችሁ ስንባል የደረሰልን አካል የለም ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት በቅርቡ አድርጌያለሁ ያለውን የደመወዝ ጭማሪ ላለፉት አራት ወራት ሊያገኙ ያልቻሉ የአካባቢው የመንግስት ሠራተኞች የተጠራቀመ የአራት ወር ክፍያቸው እንዲሰጣቸው ዛሬ አደባባይ ወጥተው በተቃውሞ ሰልፍ መጠየቃቸው ታውቋል።