ህወሃት የሠራዊት ምልመላ ለማካሄድ በየክልሉ ሌላ ዙር ዘመቻ ጀመረ

0

ህወሃት የሠራዊት ምልመላ ለማካሄድ በየክልሉ ሌላ ዙር ዘመቻ ጀመረ። በፈቃደኝነት የሚመለመል መጥፋቱ እጅግ እንዳሳሰበው ይነገራል

በመከላኪያ ሠራዊት ውስጥ ሥራ ላይ ባሉት የሠራዊት አባላት የመዋጋት አቅም ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ የገባው የህወሃት አገዛዝ አዳዲስ ምልምሎችን ለመቅጠር በመላው አገሪቱ ውስጥ ለወራት ሲያካሂደው የነበረው ዘመቻ ውጤት ባለማስገኘቱ  ሌላ ዙር የግዴታ ምልመላ እንዲካሄድ የወረዳና የገጠር ቀበሌ ካዲሬዎችን እየቀሰቀሰ እንደሚገኝ ከውስጥ አዋቂዎች የደረሰን ጥቆማ ገለጸ።

“የአርበኞች ግንቦት 7 በስውር አገር ውስጥ ያሰማራቸው ታጣቂዎች በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ተሰራጭተዋል” በሚል ስጋት አዳዲስ ምልምሎችን በብዛት ለመቅጠር ደፋ ቀና እያለ ያለው ህወሃት በአሁኑ ሰዓት አግልግሎት ላይ በሚገኘው ሠራዊት አባላት ለምን መተማመን እንዳቃተው በርካታ ምክንያቶች እየተሰጡ ናቸው ።  ከነዚህም ምክንያቶች አንዱና ዋንኛው  ህዝባዊ እምቢተኝነት በአገሪቱ ውስጥ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በርካታ የሠራዊቱ አባላት እና የበታች መኮንንኖች  ህወሃት በህዝብ ላይ የከፈተውን ጦርነት ለመዋጋት ፍላጎት እንደሌላቸው በመታወቁ  እንደሆነ ይገለጻል።

ህወሃት ጥልቅ ተሃዲሶ በሚለው ግምገማ በሠራዊቱ ውስጥ ያካሄዳቸው እንቅስቃሴዎች በትግራይ ተወላጆች  የሠራዊቱ አባላትና ከሌላው ማህበረሰብ ሠራዊቱን በተቀላቀሉ መካከል ለአመታት የቆየው አድሎአዊነት ምን ያክል አብዛኛውን የመከላኪያ ሠራዊት አባላት አስቀይሞ እንደቆየ ማረጋገጥ የተቻለበት እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች  ይገለጻሉ። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መከታ በማድረግ በአማራና ኦሮሞ እንዲሁም ደቡብ ክልሎች ተወላጆች ላይ በስፋት እየተወሰደ ያለው የሃይል እርምጃ የፈጠረው  ግድያና አፈና በሠራዊቱ ውስጥ ከፍተኛ መከፋፈልን አስፍኗልም ይባላል። በህወሃት በሚመራው የአገሪቱ መከላኪያ ሠራዊት ውስጥ ከአዛዥነቱ ቦታ ውጪ ያለውን ሠፊ የሰራዊት ብዛት የሚሸፍነው የአማራ፤ የኦሮሞና የደቡብ ተወላጆች እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህም የተነሳ ህወሃት በነዚህ ክልሎች የተነሳበትን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማክሸፍ የሚሰጠውን የአፈናና ግዲያ ትእዛዝ ሠራዊቱ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ እያቅማማ መምጣቱ አገዛዙን አስጭንቆታል። የኮማንድ ፖስቱ በአማራና በኦሮሚያ የሚሰጣቸውን ግዳጆች በመገዳደር “እኛ የተቀጠርነው አገሪቱን ከወራሪ ሃይል ለመከላከል እንጂ በገዛ ህዝባችን ላይ ለመተኮስ አይደለም “ የሚል ተቃውሞ እንዳስነሳም ይነገራል። በሠራዊቱ ውስጥ እየተንጸባረቀ ያለውን ይህንን ስሜት የተረዳው የህወሃት አገዛዝ ብዛት ያለቸውን አዳዲስ ምልምሎች በመቅጠር ነባር ሠራዊት አባላትን ቀስ በቀስ ለማሰናበት ዕቅድ እንደያዘ ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።

አሁን በሥራ ላይ ባለው የሠራዊት ስብጥር ህዝባዊ ተቃውሞው  እንደገና ካገረሸ ማክሸፍ ከባድ ሊሆን ይችላል ብቻ ሳይሆን ሠራዊቱ ከህዝቡ ጋር በመወገን መሣሪያውን አገዛዙ ላይ ሊያዞር ይችላል የሚል ከፍተኛ  ስጋት የህወሃት አመራሮችን እረፍት እንደነሳም ነው ይባላል።

በነዚህ ምክንያቶች አዳዲስ ምልምሎችን ወደ ማሠልጠኛ  ለማስገባት እንዲቻል ሰሞኑን በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ  ካድሬዎች ጋር ህወሃት ልዩ ስብሰባዎችን ተቀምጦ እንደነበር ሆኖም ግን  ከካድሬዎቹ የተሰጡ አስተያየቶች ሌላ ድንጋጤ እንደፈጠረበት ታውቆአል። ህብረተሰቡን በማሳመን የምልመላ ሥራው እንዲሳካ የማግባባት ሥራ እንዲሠሩ የተጠየቁ የህወሃት አባል ድርጅቶች አባላትና  ካድሬዎች “ ህብረተሰቡ እኛን መስማት አቁሞአልና እናንተ በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ያላችሁ ሞክሩት”  ማለታቸው ህወሃትን እጅግ አስደንግጧል እንደምንጮች መረጃ።

ከግማሽ በላይ የአገሪቱ ወጣቶች ሥራ አጥ በሆኑበት ሁኔታ ለውትድርና ሥራ ፍላጎት የሚያሳይ መታጣቱ የወረዳና ቀበሌ አመራሮች ሳይቀሩ  ውስጥ ለውስጥ የሚያካሂዱት ቅስቀሳ ውጤት ነው የሚል ውንጀላ  በደቡብ ክልል ካሉ ባለሥልጣናት አንደበት መሠማቱን የጂካ ከተማ ነዋሪዎች ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል። በመላው አገሪቱ የአዳዲስ ምልምሎች  እጥረት የገጠመው የህወሃት አገዛዝ ዘዴውን ቀይሮ በፖሊሲ አባልነት ሥም ምልመላ ለማካሄድ በተለያዩ ቦታዎች ማስታወቂያ ማውጣቱ ይነገራል።