በሳውዲ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የሚደርስልን መንግሥት አላገኘንም ይላሉ

0

በሳውዲ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የሚደርስልን መንግሥት አላገኘንም ይላሉ። ህወሃት ግን ተመላሾችን ለማጓጓዝና ለማቋቋም ግብረ ኃይል አቋቁሜአለሁ በሚል ፕሮፖጋንዳ ተጠምዷል።

ሳውዲ አረቢያ በአገሯ የተጠለሉ የውጪ አገር ዜጎችን ለማስወጣት በሰጠችው ቀነ ቀጠሮ መሄጃ እንዳጡ የሚናገሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በመንግሥት በኩል እየተደረገላቸው ያለ ምንም ዓይነት እገዛ እንደሌለ ለትንሳኤ ድምጽ ረዲዮ ገለጹ።

አገራችን ውስጥ በሰፈነው ኢፍትሃዊ አሰራር ሠርተው ለመኖር ዕድል አጥተው በባህር ወደ ሳውዲ የገቡ መሆናቸውን የሚናገሩ እነዚህ ስደተኞች እንደሚሉት፤ የጉዞ ሠነድ ለማግኘት በነፍሰ ወከፍ ከ800 እስከ 1000 ሪያል የሳውዲ ገንዘብ የተጠየቁ በመሆናቸው ለመክፈል አቅም የሌላቸው በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቀዋል።

በሳውዲ የሚኖሩ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌለው ስለሆነ ከአገር ውጡ በተባለበት በአሁኑ ሰዓት ለአውሮፕላን ቲኬት መግዣ የሚሆን ገንዘብ በእጃቸው ላይ የለም። ከአገሯ እንዲወጡ የተጠየቁ የሌሎች አገሮች ዜጎች መንግስቶቻቸው በኤምባሲዎቻቸው በኩል ባደረጉላቸው ድጋፍ ምንም አይነት ክፊያ ሳይፈጽሙ የመመለሻ አውሮፕላን ቲኬት ታድሏቸው ያለምንም ችግር እየተመለሱ መሆናቸውን እነዚሁ ስደተኞች ይገልጻሉ።

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ አገራችን ውስጥ ያለው ችግር ወደ አገር ለመመለስ የሚያጓጓ ባይሆንም ሥራ ፈተው  ለረጅም ጊዜ በየጓደኞቻቸውና በሚያውቁዋቸው ሰዎች ቤት የተጠለሉት ስደተኞች  ከመመለስ የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸው ይናገራሉ።

የህወሃት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እነዚህ በሳውዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን አስመልክቶ አርብ ግንቦት  4 ቀን 2009  ዓም ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረገው ውይይት በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታው በዶክተር አክሊሉ ገብረ ሚካኤልና የሚንስትር መስሪያቤቱ ቃል አቀባይ በአቶ መለስ ዓለም አማካይነት የሳውዲ መንግሥት የሰጠው የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ህብረተሰቡ እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ ማስተላለፈቸው ይታወቃል። ሳውዲ አረቢያ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ ካገሯ ያባረረቻቸው ኢትዮጵያዊያን ተመላሾች አገራቸው ከገቡ በወራት ጊዜ ውስጥ በሱዳን በኩል ድንበር አቋርጠው ወደ ሳውዲ ለመመለስ ጥረት እንዳደረጉ ይታወቃል።

ለትንሳኤ ሬዲዮ ከሳውዲ አስተያየቱን የሰጠ አንድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ከወራት በፊት ወደ አገር ቤት የተመለሰው ወንድሙ ወደ አገር ከተመለሰ በኋላ የጠበቀው ችግር ሳውዲ በነበረበት ወቅት ይደርስበት ከነበረው የከፋ መሆኑን ገልጾ  በመመለሱ እንደተጸጸተ መናገሩን ገልጿል። አብዛኛው የሳውዲ ስደተኛ በአገሩ ጉዳይ ተስፋ ቆርጦ የወጣ በመሆኑ ወደ አገር ቤት ከመመለስ የሚደርስበትን  ችግር እዚያው ሳውዲ ሆነው ለመጋፈጥ የቆረጠ ነውም ተብሏል።

አገር ውስጥ በዜጎች ላይ የሚደርሰው አድሎአዊነትና  አፈና በሰው አገር መሞትን የሚያስመርጥ ሆኖ እያለ ለዚህ ሁሉ ስቃይ ምክንያት የሆነው የህወሃት አገዛዝ  ግን የአገሪቱን ልማትና ዕድገት በመስበክ ፕሮፖጋንዳ ላይ መጠመዱ በርካታ የአገሪቱን ዜጎች ምሬት ጨምሮአል።