ውሻውን ከጀርባ ትተህ ከጌታው ጋር አትያያዝ (በተስፋዬ ካሳ ጎቻዬ)

ውሻውን ከጀርባ ትተህ ከጌታው ጋር አትያያዝ!!! (በተስፋዬ ካሳ ጎቻዬ)

በባሪያ አሳዳሪው ሥርአት ከባሪያዎች መሃል ተመልምለው የተለየ ጥቅም እንዲያገኙ በመደረጋቸው ከጌቶቻቸው በላይ ጌትነት የሚሰማቸው ባርያዎችን በመደብደብ በማሰቃየትና በጌቶቻቸው ላይ እንዳያምጹ በማድረግ ለሥርአቱ ትልቁን ጉልበት የሚፈጥሩት ራሳቸው ባሪያዎች ናቸው በተመሳሳይ በአንባገነን ሥርአት ከሚጨቆነው ከሚገደለውና ከሚዘረፈው ህዝብ መሃል የወጡ የይስሙላና የማያዙበት ሥልጣን ሥለተሰጣቸውና ከአብዛኛው ወገናቸው የተለየ ጥቅም በማግኘታቸው የሥርአቱ ውድቀት ከአለቆቻቸው በላይ የሚያስጨንቃቸውና ቀን ከሌት የሚባንኑ ሎሌዎች ትልቁ የሥርአቱ የጀርባ አጥንት ሆነው ማገልገልን እንደ ትልቅ ክብርና ጀብድ በመቁጠር አለቆቻቸው ካዘዟቸው በላይ በመፈጸም ታማኝነታቸው ከማሳየት በቀር ሞራል ህሊና ይሉኝታና ሰብዓዊነት ብሎ ነገር የሚጨንቃቸው ጉዳይ አይደለም።

በተለይ እነዚህ ራሳቸውን መሆን የማይችሉና በጌቶቻቸው ጫማ ሥር ራሳቸውን አስቀምጠው ያሉ ስልቻዎች የህዝቡን ሁለንተናዊ ማንነትና ምንነት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ህዝቡን ለጥቃት በማጋለጥና አውራዎቹን ነጥሎ በማስመታት ደረጃ ከዋናው ጠላት የበለጠ ሚና ስላላቸው በየትኛውም መልኩ በሚደረግ ትግል እነዚህን ከወገን ቆጥሮ መለሳለስ ትልቅ ዋጋ ከማስከፈልም አልፎ የነፃነትና የድሉ ግዜ በእጅጉ እንዲርቅ ያደርጉታልና ህወሃትን ብቻ ነጥሎ በጠላትነት ከመታገል ይልቅ ኢህአዴግ ተብሎ አብረው በተሰለፉ ላይ ይበልጥ የጭካኔን ብትር መሰንዘር ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።

የወያኔ ምልምል አሻንጉሊት ሹማምንት ወያኔ ፈቅዶና አስልቶ የህዝብ ተቆርቋሪ መስለው እንዲደሰኩሩና እንዲፎክሩ ሲያደርግ የእነሱን ወሬ ከቁም ነገር ቆጥሮ ማራገብና ማጀገን ትርፉ በሁለት ጎኑ በወያኔ የበቀል እርምጃ ለመመታት መፍቀድ ነው።አንደኛው ለወያኔ የጥላቻን ልኬት በተላላኪዎቹ ተማምኖ በማሳየት ተመንጥሮ መመታት ሲሆን ሁለተኛው ከሎሌዎቹ ለሚሰነዘር ጥቃት ራሥን አጋልጦ መስጠት ነው::
ምክንያቱም ድጋፉ በማንነታቸው ሳይሆን አለቆቻቸው ላይ በመፎከራቸው በመሆኑ አለቆቻቸውን የጠላ ትዛዝ ፈጻሚዎቹን ወዳጅ አድርጎ እንደማይቀበል የሚያውቁት ሃቅ ነውና። ወያኔም ከጎኑ ያሉትም በሃቅ ከውስጥ ሆነውም ሆነ ከወያኔ ተፋተው ከህዝብ ጎን መሰለፋቸውን የምናረጋግጥበት ተግባር እስካልከወኑ በባንዳ መበላት ብቻ ነው ትርፋችን። መቼም ቢሆን ጥርሱ ቢራገፍ እንኴን ውሻ ያጎረሰ ጌታውን በድዱም ቢሆን መናከሱን አያቆምም።-