በሰላም ደኅንነትና ልማት ለጥፋት ከተጋለጡ 178 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠች

0

አባይ ሚዲያ ዜና
አቤኔዘር አህመድ

Fund for peace የተሰኘው ተቋም በሃገራት ሰላም፣ ደኀንነትና፣ ልማት ላይ ያተኮረውን ዓመታዊ ዘገባውን ይፋ አድርጓል። ሪፖርቱ የሰብዓዊ መብትና ደኅንነት አያያዝ፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ የሰዎች መፈናቀልና መሰደድ፣ በየሃገራቱ ያለው የህግ ማዕቀፍ፣ ማህበራዊ አገልግሎትና ጠቅላላ ብሶቶችን እንደሚያጠቃልል የድርጅቱ የፕሮግራም ኃላፊ ሃናሃ ብላዝ ተናግረዋል። 

በዚህ ዓመታዊ ዘገባው ደቡብ ሱዳንን በከፍተኛ ደረጃ ለጥፋት የተጋለጠች በማለት ከ178 ሃገራት አንደኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጣት ኢትዮጵያን 15ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። ኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻለችበት ምክንያት የደኀንነትና የልማት ዋስትናዋ በጣም ደካማና እየተባባሰ በመምጣቱ መሆኑን ዘገባው ይጠቅሳል። በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የነበሩ ተቃውሞዎች የሰብአዊ መብትና የሰዎች ደኅንነት አያያዝን አስከፊና እንዲባባስ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ መንግስት ሃገሪቱ ያለችበትን ደረጃ ለማማሻሻል የሰብአዊ መብት ይዞታዎችን የማሻሻል ፖለቲካዊ ፍቃደኝነት ሊኖረው ይገባል የሚሉት ዳይሬክተሯ የኢትዮጵያ መንግስት ግን በሰብአዊ መብትና በህዝብ ደኅንነት ጥበቃ ላይ ያተኮሩ ይህን መሰል ዘገባዎች የሚያወጡ ተቋማትን «ፀረ-ሰላም እና ፀረ-ልማት» ሲል ይወነጅላቸዋል። ብላዝ መንግሥት አጥኚ ተቋማትን ከሚወቅስ ይልቅ ችግሮቹን ለማሻሻል እንዲጥር መክረዋል።