የአሜሪካ የሁለቱም ፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የኢትዮጵያ መንግስትን የሚኮንን የህግ ውሳኔ ሰነድ አቀረቡ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ጋሻው ገብሬ

ዛሬ እሮብ ሜይ 17፣ 2017 በዋሽንግተን  ዲሲ የአሜሪካ የሁለቱም ፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የኢትዮጵያ መንግስትን የሚኮንን የህግ ውሳኔ ሰነድ ለከፍተኛው ምክር ቤት አቅርበዋል።

የአሜሪካ ከፍተኛ ምክር ቤት (ሴኔት) አባላት የሜሪላንድ ስቴቱ ሴናተር ቤን ካርዲን እና የፍሎሪዳው ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ የዴሞክራት እና የሪፑብሊካን ፓርቲዎች ለአሜሪካ ከፍተኛ ምከር ቤት የህግ ውሳኔ ሰነድ በጋራ አቅርበዋል።

የህግ ውሳኔው ሰነድ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ መንግስት የፖሊስ ሰራዊት እጅግ ከመጠን ያለፈ ሃይል (ዱላ፤ ጥይት) በመጠቀም በ2016 በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ተጠያቂ ያደርገዋል። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ መታሰራቸውንም ያስታውቃል።

የህግ ውሳኔው ሰነድ የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን ተቃዋሚዎችን አክቲቪስቶችን ጋዜጠኞችን ሁሉ እንዲፈታ ይጠይቃል። በህገ መንግስቱ የተደነገገውን መብት እንዲያከብርም ይጠይቃል።

ህዝብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተቃውሞውን ሲያሰማ ለሞትና ለእስራት ተዳረገ ይላል የውሳኔ ረቂቁ።

ሴናተር ቤን ካርዲን እና ሴናተር ማርኮ ሩቢዮን የተባበሩት ሌሎች ህግ አውጭዎች፣ ሴናተሮች፣ ቶማስ ቲሊስ (ሪፑብሊካዊ) ኖርዝ ካሮላይና፣ ሮን ዌይን (ዲሞክራት) ኦሬጎን ስቴት ዲክ ደርቢን (ዲሞክራት) ኢሊኖይ ስቴት፤ ጆን ኮራይን (ሪፑብሊካዊ) ቴክሳስ፤ዴቢ ስታቤናው (ዲሞክራት) ሚቺጋን ስቴት ክሪስ ኩንስ(ዲሞክራት) ዴላዌር፣ ኮሪ ጋርድነር (ሪፑብሊካዊ) ኮሎራዶ፣ ኮሪ ቡከር (ዲሞክራት) ኒው ጄርሲ፣ ሼራድ ብራውን (ዲሞክራት) ኦሃዮ፣ አል ፍራንኬን (ዲሞክራት) ሚኔሶታ፣ ክሪስ ቫን ሃላን (ዲሞክራት) ሜሪላድ እና ጄፍ ሜርክሌይ (ዲሞክራት) የኦሬጎን ስቴት ናቸው።

ቤን ካርዲን ሲናገሩ “የኢትዮጵያ መንግስት ሰብአዊ መብቶችን ለማክበር የመሻሻል መንገድ ማሳየት እና ዴሞክራሲያዊ ነጻነትን ማክበር ይኖርበታል። ዛሬም እውቅ የፖለቲካ መሪዎች በእስር ላይ መሆናቸው እጅጉን ያሳዝነኛል። ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሽብርተኛን በጋራ ለመዋጋት ስምምነት አለን ማለት ህዝብ ሲበደል ዝም ብለን እንቀመጣለን ማለት አይደለም።” ብለዋል። ቤን ካርዲን የሴኔቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ከፍተኛ አባል ናቸው። በአንጻሩ አሉ ቤን ካርዲን “ወዳጅነታችን ንጹሃን ሲበደሉ፣ ሲታሰሩ አዋጆች ሰላማዊ ተቃውሞን ማፈኛ ሲሆኑ እንድንናገር የግድ ነው” ይላሉ።

ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ ደግሞ “የኢትዮጵያ መንግስት ሰብአዊ መብቶችን ለማክበር የመሻሻል መንገድ መያዝን ሲለግም፣ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ መምጣት ሳይመች ሲቀር ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ድምጿን ከፍ አድርጋ የኢትዮጵያ መንግስት ሰብአዊ መብቶችን እንደረገጠ፣ ህዝብንም መበደሉን እናወግዛለን” ብለዋል። ሴናተር ማርኮ ሩቢዮም የሴኔቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ከፍተኛ አባል ናቸው። ሩቢዮ ሲያጠቃልሉ ”በከፍተኛው የህግ መወሰኛ ምከር ቤት የምንገኝ እኔና ባልደረቦቼ የኢትዮጵያ መንግስትን አጥብቀን እንጠይቃለን። ፍተህ ርትእን አክብሩ፣ ሰብአዊ መብት ላይ አትኩሮት ይኑራችሁ፣ ፖለቲካዊ ለውጦችን ቀዳሚነት ስጡ እንላለን” ብለዋል።