ዘመንም እንዲህ ያረጃል። ወርቃማውን የክርስትና ዘመን እንናፍቃለን ( በመስቀሉ አየለ )

በደደቢቱ ማኔፌስቶ የተቀመጠውን ኦርቶዶክስን የማፍረስና ምንፍቅናን የማንገሱ ሴራ በከፋ መልኩ ቀጥሏል። ከአለም ዙሪያ ካሉና ጉዳዩ ስጋት ላይ ከጣላቸው በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ምእመምናን የአዲስ አበባውን ቅዱስ ሲኖዶስ በስልክ፣ ኢሜይልና በማህበራዊ ድህረገጾችን በመጠቀም ርብርብ ቢያደርጉም ሲኖዶሱ ጆሮ ዳብ ልበሱ ብሎ አንዱን በብልግናው የማይታማ፣ የስብሃት ነጋ የመንፈስ ልጅ የሚሆን ነውረኛ ኢ-ኦርቶዶክሳዊ ፓስተር እና አንድ ልማታዊ “መነኩሴ” ደግሞ በቀጥታ ከጋምቤላው አስተዳዳሪ በተጻፈ የትዕዛዝ ደብዳቤ “ለጵጵስና” ሹመት አቅርቧቸዋል።

ከስልሳ ሚሊዮን ያላነሰ ምዕመምን ያላት ቤተክርስቲያን ታዛቢ እንደሌለው ቤት ማንም ከምንም ተነስቶ ወደ ላይኛው መንበር የሚሰቀልባት ሆናለች። ይኽ ሁሉ ሲሆን ደግሞ ለተወሰኑ ቀናት ከንፈር ከመምጠጥ ውጭ የተጨበጠ ተቃውሞ የሚያደርግ ወይንም ለቤቱ የሚቀና ቆፍጣና ወጣት የለም። “የቤትህ ቅናት በላኝ” ተብሎ በወንጌል የተጻፈውንና ባለቤቱ ስለ ቤቱ ጉዳይ ባለው ክብር ሸቃጩን ሁሉ በጅራፍ እየገረፈ ስለማውጣቱ የተነገረው አይመስልም። ወያኔ እንደ እነዳንኤል ክብረትን በመሰሉ ከገዥው መደብ ጎሳ ጋር የጋብቻ ዝምድና ከፈጠሩ ልማታዊ ሰባኪያን በተቀመረ ዘዴ “ይዘን መጣን” ባሉት አዲሱ የስብከት ዘዴ አንድ ሙሉ ፓሲቭ (ምውት) ጀነሬሽን የመፍጠሩ ሂደት እንደተሳካላቸው በፍሬው ይታወቃል። በአንድ ወቅት ከወያኔ ተሰርቆ በወጣው ዳጎስ ያለ ጥናት ላይ ሰፍሮ እንደተገኘው “ወጣቱን ከነቴዲ አፍሮ አይነት አስተሳሰብ በማውጣት በተጠና መንገድ ወደ እነ ዳንኤል ክብረትን መንገድ መግፋት..” የሚል እንደነበር በኢሳት ቴለቪዥን ተለቆ ያየነውን ሃቅ ልብ ይሏል።

-አገሬ በሰማይ ነው የሚል፤

-ሁሉም ነገር በሃጢያቴ ብዛት የመጣብኝ ችግር ነው የሚል፤ እግዚአብሔር ያውቃል በሚል ሽፋን ተጀቡኖ ለራሱ ሃላፊነትን የማይቀበል፤

-በአገሩ ጉዳይ ያገባኛል ማለትን እንደ ሃጢያት የሚያይ፤ ምንም ይሁን ምን ንጉስ የሚነግሰው በእግዘ አብሔር ፈቃድ በመሆኑ እርሱን ማውረድም ሆነ ማስቀጠል የእግዚ አብሔር ድርሻ በመሆኑ የኔ ድርሻ ነገስታቶችን ልብ እንዲሰጣቸው መጸለይ ብቻ ነው ብሎ ከልቡ የሚያምን፣

-ነጠላ ለብሶ ጧፍ ስላበራና ከበሮ ስለመታ ብቻ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት የተወጣ የሚመስለው፤ የተሰለበ ትውልድ የመፍጠሩ ሂደት በተወሰነ ደረጃ አልተሳካም ማለት አይቻልም። ይልቁንም ቤተክርስቲያን ባንድ እጇ መስቀል በሌላኛው ሰይፍ ታጥቃና ሲያስፈልግ ታቦት ጭምራ ይዛ ጦር ስታዘምት የነበረበችትን ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ የሆነውን አስተሳሰብ ሆነ ብለው በረቀቀ ዘዴ ከውስጡ እንዲጨነግፍ አድርገውታል፤ ድህረ ደርግ ብቅ ያሉት ሰባኪ ወንጌላውያን ነን ባዮች።

ኢትዮጵያዊ ሲባል ብዙ መነገር መገዘት ሳያስፈልገው “በሚስትህ በልጅህ እና በሃይማኖትህ የመጣውን ወራሪ ለመመለስ ፋኖ ውረድና አግዘኝ፤ ይኽን ሰምተህ የማትመጣ ብትኖር ማርያምን ትጣላኛለህ..” በምትል አንዲት ቃል እንደ ንብ ይተን የነበረውን ያን ቤተክርስቲያኑን ከአገሩ ለይቶ የማያይ የነበረውን ኩሩ ዜጋ በተጠና የስብከት ዘዴ “አገሬ በሰማይ ነው” የሚልና ድርሻውን የማይወጣ፤ ይህ ሁሉ ድፍረት በአገርና በቤተክርስቲያን ላይ ሲፈጸም ከንፈሩን ብቻ የሚመጥ ወይንም ጨርሶ የማይቆጭ እንግዳ ዜጋ ፈጥረዋል። ዛሬ ቤተክርስቲያንን በማዘመን ሽፋን በተሃድሶ ስም ፣ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያላትን በእትብት የተገመደ ትስስር አውልቃ የጣለች፣ ህይወት አልባ፣ ታሪክ አልባ በማድረግ የነጮች ቆሻሻ አስተሳሰብ የሚደፋባት ተቋም ለማድረግ ይህ ሁሉ ውንብድና በቀን ብርሃን ሲፈጸም ውስጥ ውስጡን ከሚብገነገን በቀር ምንም ማድረግ የማይችል መንፈሱ ሽባ የሆነ ትውልድ ፈጠሩ እነ ዳንኤል ክብረት።መራራውን ሃሞቱን እንደ ስእል በተሳለ አማረኛ እንደ ስኳር ጣፋጭ ላደረጉበት፤ መንፈሳዊ ወኔውን ላስጣሉበት ባገኙት ዳረጎት እነርሱ ዛሬ የሃብት ሰገነት ላይ ወጥትዋል። ዛሬ በአዲስ አበባ እንዲህ እየሆነ ነው።

ግዜያዊው መፍትሔ!

በአንድ ሰሞን ተጀምሮ የነበረው የጎንደርና የጎጃምን አብያተ ክርስቲያናት ከፓትሪያሪኩ ቁጥጥር ውጭ የማድረጉን እርምጃ እንደገና ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ እርምጃውን ወደሌሎች ክልሎችንም እንዲያካትት ማድረጉ አማራጭ የሌለው ነገር ነው።