ዶናልድ ትራምፕ በተጋበዙበት የሳውዲው የእስልምና ሰሚት ላይ የሱዳኑ መሪ እንደማይካፈሉ ተገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር በሳውዲ አረቢያ በሚደረገው የእስልምና ሰሚት ላይ መሳተፍ እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል።

በዚሁ ስብሰባ ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በክብር እንግድነት ተጋብዘዋል።

ለዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝዳንትነትን በትረ ስልጣን ከጨበጡ በሃላ ይህ የመጀመሪያው የውጭ አገር የስራ ጉብኝት እንደሆነም ተዘግቧል።

የዶናልድ ትራምፕ በዚሁ ስብሰባ ላይ በክብር እንግድነት መጋበዝ ለኦማር አል በሽር አለመገኘት ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ተሰጥቷል።

በስብሰባው ላይ ለመገኘት ባለመቻላቸው የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ለሳውዲው ንጉስ በጽሁፍ ይቅርታ እንደጠየቁ ከኦማር አል በሽር ቢሮ ከተሰጠው መግለጫ መረዳት ተችሏል።

በሪያድ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ለመገኘት ያልቻሉበትን ዝርዝር ምክንያት ግን አልተገለጸም።

ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር በዘር ማጥፋር ወንጀል ክስ በአለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ የሚፈለጉ መሆናቸው ይታወቃል።

በእሳቸው ምትክ የአገሪቷ ሚኒስትር ታሃ አል ሁሴን ወደ ሳውዲ በመብረር ስብሰባውን እንደሚካፈሉ መረጃዎች ያሳያሉ።