የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህጋዊነት ተመዝግበው ከሚንቀሣቀሱ 62 የፖለቲካ ፖርቲዎች መካከል በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የህግ ጉዳዮችን ያሟሉት 10ሩ ብቻ ናቸው አለ

አባይ ሚዲያ ዜና

አሰግድ ታመነ

በቦርዱ በህጋዊነት ተመዝግበው ከሚንቀሣቀሱ 62 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሀገር አቀፍ ሲሆኑ፣ 40ዎቹ ክልላዊ ናቸው፡፡

ከመካከላቸው 52ቱ ፓርቲዎች በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅና መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የህግ ጉዳዮችን አላሟሉም ብሏል ቦርዱ፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ መቃና እንዳሉት ህጐቹን በከፊል ብቻ አሟልተዋል ካሏቸው 52 ፓርቲዎች 4ቱ ጠቅላላ ጉባዔ አላካሄድም፣ በህጉ መሠረት አዲስ አመራር መርጠው አላሳወቁም፣ የውጭ ኦዲተር አልሾሙም፣ ወቅታዊ ሪፖርት አላቀረቡም፣ የፅህፈት ቤታቸውን አድራሻም አላሳወቁም ብለዋል፡፡

 

በተያያዘ ቦርዱ በፌዴራል ወይም በክልል ምክር ቤቶች ውክልና ላላቸው 7 የፖለቲካ ፓርቲዎች ለማከፋፈል በ2008 ዓ.ም 10 ሚሊዮን ብር ከመንግሥት አስፈቅዶ እንደነበር ሰብሳቢው አስታውሰዋል፡፡

ቦርዱ ገንዘቡን ያከፋፈለው ግን ከኦዲተር የተረጋገጠ ሪፖርትና ደረሰኝ አቅርበዋል ላላቸው 3 ፓርቲዎች ብቻ መሆኑን ሰምተናል፡፡

ከ10 ሚሊዮን ብሩ፤ ከ7 ሚሊዮን 339 ሺ ብር በላዩን ለገዢው ፓርቲ ለኢህአዴግ እንደተሰጠው የምርጫ ቦርድ ሰብሣቢ ተናግረዋል፡፡

ሰብሣቢው የቦርዱን የ9 ወር ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንደሰማነው ለእለት ተእለት ተግባራቸው ከ10 ሚሊዮን ብሩ የመከፋፈል እድል ከደረሳቸው 3 ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢሶህዴፓ/ ከ1 ሚሊዮን 298 ሺ ብር በላይ ተሰጥቶታል ተብሏል፡፡

የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አብዴፓ/ ከ352 ሺ ብር በላይ በባንክ ሂሣብ ቁጥሩ ገቢ ተደርጐለታል ብለዋል ሰብሣቢው፡፡

በፌዴራል ወይንም በክልል ምክር ቤቶች ውክልና ካላቸው 7 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመደገፍ ቦርዱ ከተፈቀደለት 10 ሚሊዮን ብር 4 ፓርቲዎች ቅድመ ሁኔታዎችን አላሟሉም ተብለው ምንም ክፍያ አልተፈፀመላቸውም ተብሏል፡፡

ፕሮፌሰር መርጋ በመጪው ዓመት ለሚካሄደው የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶችና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደውን የአካባቢ ምርጫ ለማስፈፀም የዝግጅት ሥራዎችም መከናወናቸውን በሪፖርታቸው አካተው አቅርበዋል፡፡