26 የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በግብጽ አገር ተገደሉ

አባይ ሚዲያ ዜና
ጋሻው ገብሬ

ዛሬ አርብ ጭንብል የለበሱ ታጣቂዎች ክርስቲያኖች ጭኖ የሚሄድ አውቶቢስ ጥቃት ደርሶበት 26 ሰዎች ሞተዋል።

ፍራንስ 24 ዓለም አቀፍ የፈረንሳይ ዜና አውታር እንደዘገበው ዛሬ አርብ ቀን ከርስቲያኖቹ ወደ ካይሮ ደቡብ የሚገኝ ገዳም ባውቶቢስ ሲጓዙ በታጣቂዎች በተሰነዘረ ጥቃት ሞተዋል። የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች (ኮፕትስ) በመካከለኛው ምስራቅ ጥንታዊና በእስልምና ተከታዩ መካከል የሚገኙ ባንድ ስፍራ ብዛት ያለቸው የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ህብረተሰብ ናቸው።

ግብጽ 90 ሚሊዮን ህዝብ አላት። ከዚህ ቁጥር አስር እጁ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ነው።

የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች (ኮፕትስ) ታሪካቸውን ከክርስትና ሃይማኖት መሰበክ መነሻ ጀምሮ እንደሆን ይጠቅሳሉ። በዚያን ዘመን ግብጽ የጥንቱ የሮማንውያን ሰፊ የዓለም ግዛት አንዷ ክፍል ነበረች። ኋላም የባዛንቲዩም (ቱርክ) ሰፊ የዓለም ግዛት አንዷ ክፍል ነበረች።

ኮፕት የሚለው ስያሜ ለግብጾቹ ክርቲያን የወጣው “ኮፕት” ማለት በጥንታዊ ግሪክ ቋንቋ ግብጻዊ ማለት ስለነበር ነው።

የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች (ኮፕትስ) ህብረተሰብ እየወደቀ የመጣው በ7ኛው ክፍለ ዘመን አረቦች እስልምናን ሲያስፋፉ ነው። ዛሬ ግብጽ በአብዛኛው የሱኒ እስልምና ተከታዮች አገር ናት።

የግብጽ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች (ኮፕትስ) በሁሉም የግብጽ የህብረተሰብ መደቦች ውስጥ ይገኛሉ። በአብዛኛው የሚኖሩት መካከለኛውና ደቡብ የግብጽ ግዛት ነው። ከመንግስት የስልጣን አላፊነት የተገለሉ ናቸው። በዳኝነት፤ዩኒቬርሲቲዎች እና ፖሊስ የአላፊነት እንዳያገኙ በሹመት ጊዜ ይዘለላሉ። በየጊዜው ከቅርብ አንስቶ የደረሰባችው በደል እንደሚከተለው ነው።

ሜይ 2011 ደግሞ በክርስቲያኖችና የሙስሊሞች ግጭት አንድ ኢምባባ በተባለ የካይሮ ክፍለ ከተማ 15 ሰዎች ሞተዋል። በኦክቶበር ወር ደግሞ 30 ሰዎች ሞተዋል። አንዛኞቹ ኮፕቶች ነበሩ። ይህ የሆነው የግብጽ የጦር ሰራዊት ቤተ ክረስቲያን ተቃጠለ በማለት ባስነሳው ተኩስ ነው።

2011 ህዝባዊ አመጽ ተነስቶ አምባገነን ሆስኒ ሙባራክ ካሰናበተው በኋላ በተደጋጋሚ ኮፕቶች የጥቃት ሰለባ ሆነዋል። ጃንዋሪ 1, 2011 ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተጣለ ቦምብ 20 ሞተዋል።

ጁላይ 2013 ሆስኒ ሙባራክ ተሰናብቶ ሞሃመድ ሞርሲ ስልጣን ሲይዝ በአመቱ በክርስቲያኖች ላይ ጥቃቱ ቀጠለ። ሞሃመድ ሞርሲ ከስልጣን ሲወገድ የርሱ ደጋፊዎች ኮፕቶቹን ለመወገዱ ምክንያት እናንተ ናችሁ በሚል አጠቋቸው። ሞርሲ ስልጣን ሲለቅ በተከተሉት ሳምንታት 40 ቤተ ክረስቲያኖች በግብጽ ውስጥ መቃጠላቸውን ሰባአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ህይማን ራይትስ ዋች ተናግሯል።

በ2016 ዲሴምበር ወር የአይሲስ ሽብርተኛ አጥፍቶ ጠፊ 29 ሰዎች የሰንበት ጸሎት ሲያደርሱ በካይሮ ገድሏል። በሲና በረሃም በሚደርሰው ጥቃት የኮፕት ቤተ ሰቦች መኖሪያ ቀያቸውን ለቀው እንዲሄዱ አክራሪ እስላም የሆኑ ሀይሎች አድርገዋል።

እስላማዊ መንግስት የተባለው አሸባሪ “ክርስቲያኖችን አጥቁ” የሚል ቪዶዮ ካሰራጨ በኋላ 250 የሚሆኑ ክርስቲያኖች እስማኢሊያ በተባለችው የስዌዝ ካናል ከተማ እዲሸሸጉ ተገደው ነበር።

ኤፕሪል አስራ አንድ በዚህ ዓመት በካይሮ ሁለት ቤተ ክርስቲያኖች ጥቃት ደርሶባቸው 45 ሰዎች ሞተዋል። ይህ በክርስቲያኑ ላይ በግብጽ ከደረሱት ጥቃቶች ትልቁ ነው።

ዛሬ አርብ ጭንብል የለበሱ ታጣቂዎች ክርስቲያኖች ጭኖ የሚሄድ አውቶቡስ ጥቃት ደርሶበት 26 ሰዎች ሞተዋል።

ኢትዮጵያ አገራችን ከግብጽ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች (ኮፕትስ) ጋር የጋራ ታሪክ አላት። በሃይማኖት ምክንያት የሚነሳ ግጭት ለአገር ጠንቅ እንደሆን ግብጽ ምሳሌ ናት። ከግብጽ መንግስት ክረስቲያኑን ከጥቃት ለማዳን እንዲጥር ሰባአዊ መብት ተሟጋቾች እየወተወቱ ነው።