ቴዲ አፍሮ በአምስተኛው ከፍታ ላይ ዘውድ የጫነበት ምስጢርና የተሰጠው ታላቅ ተልእኮ (በወንድወሰን ተክሉ)

ወንድወሰን ተክሉ

የሃያሉ ኢትዮጵያዊነት ሀይል እና የሃያሉ የፍቅር ሀይል መገለጫ ክስተት የሆነው ኢትዮጵያዊው አርቲስት ቴውድሮስ ካሳሁን [ቴዲ አፍሮ]በ40ኛ ዓመቱ በአዲስና በታላቅ ታሪካዊ ምእራፍ ላይ የተገኘ ልጅ ሆኖ ተገኝታል።  ይህ ዛሬ የደረሰበትና -ሀ-ብሎም የጀመረው አዲሱ የህይወቱ ምእራፍ ልዩ ተልእኮ እና ታላቅ ሃላፊነትንም አካቶ ያቀረበለት መሆኑን አስተውለናል። ልጁ ለዚህ የበቃበትን እና ብሎም ለዚህ ያበቃውን ምስጢር እና የሚጠብቀውን ሃላፊነት እያነሰሳሁ በማመላከት የእኛንም ግላዊም ይሁን ድርጅታዊ ብሎም አገራዊና ቤተሰባዊ ሚናን እየለየን በማየት መወጣት እሚገባንን ድርሻና ሃላፊነት የምንወጣብትን ስፍራና አቅጣጫም ለማሳየት እጥራለሁ።

1ኛ) የንግስናው አስካል-

አርቲስት ቴዲ አፍሮ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ቀደምት ገናና አርቲስቶቻችን እነ ጋሽ ጥላሁን ገሰሰ፣ አስቴር አወቀ፣መሀሙድ አህመድ፣ሙሉቀን መለሰ፣አለማየሁ እሸቴ…ወዘተ የመሳሰሉት መድረስ ያልተቻላቸው ከፍታ ማማ ላይ በክብር መገኘት የቻለ ድንቅ ልጅ  ሆናል፡፣ በ1980ዎቹ ታላቅ ታዋቂነትን ተቀዳጅታ የነበረችው አስቴር አወቀ በካቡ አልበማ እነ ቢቢሲና ቪኦኤን ጨምሮ በአብዛኛው የዓለም መገናኛ ብዙሃን ሽፋን የተሰጣት ቢሆንም በሙዚቃ ሽያጭ ቻርት [ቢል ቦርድ] ላይ ግን የመሪነቱን ስፍራ ልትቀዳጅ አልቻለችም ነበር። ቴዲ አፍሮ ግን በ5ኛ እና “ኢትዮጵያ “ብሎ በሰየመው አልበሙ ውቂያኖስ ተሻግሮ አህጉር አቆራርጦ በዓለም የሙዚቃ ቻርት [ቢል ቦርድ] ላይ የታወቁ ዓለም አቀፍ ዝነኛ አርቲስቶችን አንደኝነት ደረጃ በክብር አስልቅቆ ለመያዝ የቻለ ብቸኛውና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አርቲስት ሆናል። እዚህጋ- ቴዲን ከላይ ከጠቀስካቸው ብርቅ እና ድንቅ አርቲስቶቻችን ጋር በማነጻጸር ወይም በማወዳደር ቴዲሻን ከፍ ክፍ እያደረኩ ሌሎቹን ደግሞ ዝቅ ዝቅ እያደርኩ እንደሆነ ተደርጎ እንዳይወሰድብኝ በጥብቅ ልገልጽ እወዳለሁ። እያንዳንዱ ትውልድ የየራሱ የሆነ የጥበብ ንጉስ እንደሚያፈራ ይታወቃል።የእኔና መሰል የዛሬው ትውልድ የጥበቡ ዓለም የነገሳታት ንጉስ ቴውድሮስ ካሳሁን ብቻ እና ብቻ መሆኑን በእኛ ፍላጎት ሳይሆን በአንጋሹ የጥበብ፣የፍቅርና የሁሉ ስነ-ፍጥረት ምንጭ በሆነው ሃያሉ ሃይል በ5ኛው የከፍታ መድረክ ላይ ዘውድ ጭኖለት የነገሰ ልጅ ሆናል። “እንግዲህ እናንተ የሰቀላችሁትን እሱ እግዚአብሔር አብ ከሙታንም አንስቶ በዙፋኑ ቀኝ በማስቀመጥ በህያዋን እና በሙታን ላይ የሚፈርድ አምላክ አድርጎ አንግሶታል” እንዳለው ሃዋሪያው ጳውሎስ ስለ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ- እኔም ስልጣን፣ጥበብ፣ሞገስና ክብር ሁሉ ከላይ ከሰማይ የሚሰጥ ነውና ቴዲ አፍሮን ለማዳከም ብላችሁ ስታጠቁት የነበራችሁ የዘመናችን ባለመሳሪያ ገዢዎችና የጥላቻ መንፈስ ሰለባዎች ሁሉ ብትወዱም ባትወዱም-ቢመራችሁም ሆነ ቢጥማችሁ [በጣም እንደመረራችሁ እናውቃለን]አርቲስት ቴውድሮስ ካሳሁን አንዳችም ወታደርና መሳሪያ የሌለው ልጅ ሃያሉ የፍቅር ሃይል እና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ሙዚቃ ብሎ በክፍታ ላይ የንግስናውን ዘውድ በዓለም ፊት ጭኖ አንግሶታልና እርማችሁን አውጡ እላችሃለሁ።

5ኛው አልበሙ “ኢትዮጵያ” ለቴዲ አፍሮ የንግስና ዘውድ ምክንያት ቢሆንም መሰረቱ የተጣለውና ለንግስና የታጨው ልጁ ቀደምት በሰራቸው 4ት አልበሞቹና ከ20የብሚበልጡ [በጣም ለመታረም ዝግጁ ነኝ የቁጥር ስህተት ከፈጠርኩ]ነጠላ ስራዎቹ እንደሆነ መረዳት ይኖርብናል። ቴዲ አፍሮ ከ1993ቱ የመጀመሪያ አልበሙ አቡጊዳ [በእርግጥ ከአቡጊዳ አልበም መለቀቅ በፊት አንድ አልበም ቴዲ ሰርቶ የነበረ ቢሆንም አሳታሚው ሙዚቃ ቤት ከ2ዓመት በላይ ለገበያ ባለማቅረቡ የተነሳ አቡጊዳ እንደ የመጀመሪያው ከህዝብ ጋር መተዋወቂያ አልበሙ ሆኖ ለገበያ የበቃ መሆኑንም ግንዛቤ ላስይዝ እወዳለሁ]ስራዎቹን ጭምቅና እጥር አድርገን ስናየው
የልጁ ስራ-
*ፍቅርን በዋንኝነት ደረጃ
*ውበት፣የፈጠራን ተክለሰውነት፣መቻቻል፣ታማኝነት፣እውነትና ሃላፊነትን….
*ታሪክ፣ባህል፣አንድነት/እርሰበርስ መተባበር…
*ኢትዮጵያዊነትን፣ኢትዮጵያዊ ማንነትን እና ኢትዮጵያዊ አንድነትን መሰረት ያደረጉ መልእክቶችን በረቀቀ፣ማራኪና መስህብ ባለው ተደማጭነትን በፈጠረ አቀራረብ ሲገልጽ የነበረ እንደሆነ ከስራዎቹ ስነ-ባህርይ ተነስተን መረዳት እንችላለን። የእነዚህ መልእክቶች መነሻ ምንጭም ዋነኛውና ሃያሉ ፍቅር እንጂ ሌላ ሀይል እንዳልሆነ ከመልእክቶቹ ትርጉማዊ ባህሪይ መረዳት እንችላለን።

ሆኖም 5ኛውና ኢትዮጵያ ብሎ የሰየመው አልበሙ የንግስናውን ዘውድ ለቴዲ በክብር ያመጣለት በመሆኑ ዋናውን ሚና የተጫወተ ስራው ሆኖ እናገኘዋለን።

ባለ 14ቱ 5ኛው ኢትዮጵያ አልበምን በግርድፍ እይታ ስናየው-
1ኛ- ከመጠሪያ ስሙ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትን እና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በጉልህና ብውብ አገላለጽ ጥንታዊነታችንን እያጣቀሰ የገለጸበት ስራ -ከእስከዛሬው ስራዎቹ ልቆና ተወዶ የተገኘበት ምስጢር የኢትዮጵያዊነትን መንፈስና ገጽታን በዋነኝነት ይዞ በመገኘቱ ነው።

2ኛ-ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት-

ቴዲ አፍሮ በአንደበቱ በገለጸው አገላለጽ “በከፍተኛ አደጋ” ላይ በሚገኝበት በዚህ ወሳኝ ምእራፍ -ይህው ላለፉት 25ት ዓመታት በከፍተኛ ጥቃት ስር እየተጠቃ ያለው አይበገሬውና እማይሸነፈው ሃያሉ የኢትዮጵያዊነት መንፈስና ስም ቴዲን ከኢትዮጵያም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን በማጎናጸፍ ልጁን ለንግስና ዘውድ ሲያበቀው ለማየት ችለናል።

3ኛው-ባለ 14ቱ 5ኛው ኢትዮጵያ አልበም እንደሰሙ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን በ4ት ቃንቃ ያቀረበበት ብቸኛውና የመጀመሪያው ስራው እንደሆነም ከግንዛቤ ውስጥ የምናስገባለት ተግባር ነው። ይህ ድንቅ ጥበባዊ፣መንፈሳዊ፣ታሪካዊና ባህላዊ ቅንብሩ ሃያሉ የኢትዮጵያዊነት መንፈስና ሃያሉ የፍቅር ሃይል-በአገሩ ወቅታዊ መንግስት ኮንሰርቶቹ እየተሰረዙበትና እየታገዱበት የተጎዳው-ህዝብ የወደዳቸውን ዘፈኖቹ [እንደ ጃ-ያስተሰርያል፣ጥቁር ሰው፣ዳህላክ..ወዘተ]በሕዝብ የመገናኛ ብዙሃን እንዳይቀርቡ እየታገዱበት የተቸገረውን አርቲስት ቴውድሮስ ካሳሁንን ቤተኛው ያላከበረውን ደጀኛው ያነግሰዋል እንደተባለው የንግስናውን ዘውድ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ እንዲነግስ አድርጎታል። ዛሬ ቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ ፕሪስሊ ወይም ኢትዮጵያዊው ማይክል ጃክሰን የሆነ የሙዚቃው ዓለም ንጉሰ ነግስት ነው።

2ኛ) የንግስናው አስካል መፈጠሪያ ስብእናው-  የልጅ ቴዲ አፍሮ ስብእና ለጥበብ አማልእክቶችና ለፍቅር አምላክ ሃያል ሃይል ማደሪያነት የሚመረጡ ምቹ ስብእናንም የተጎናጸፈ መሆኑ ዛሬ ለደረሰበት የከፍታ ማማ መሰረት ሆኖታል። 27 ደቂቃ በፈጀው የቪ.ኦ.ኤ ቃለመጠይቅ ቴዲ አፍሮ ከ15ግዜ በላይ የእግዚአብሔርን ስም ጠርታል። ከጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ለቀረበለት ግለ ጥበባዊ ክህሎቱን ለመግለጽ ለሚጥቅሙ ጥያቄዎች ቴዲ ከ10በላይ ባለውለታ ባለሙያዎችን ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ እና ሃያሉን እግዚአብሔር ደጋግሞ በመጥራት በማመስገን የውጤታማነቱን መንስኤ ከእኔነቴ አገላለጽ አውጥቶ ለሌሎች አጋርቶ በመስጠት ሲመልስ ተስተውላል። እንዲያውም “ይህ የእግዚአብሔር ድል ነው። ኢትዮጵያዊነት በዓለም መድረክ ላይ መጠራቱ የእግዚአብሔር ስራና የአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውጤት ነው” በሚል ሲመልስ ተሰማ እንጂ “እኔ እንዲህ አድርጌ..እኔ እንዲህ ተፈላስፌ..” ሲል አልተሰማም። ምስጋና እና የሌሎችን አስተዋጽኦ እውቅና መስጠት ከፍቅር ህግጋቶቹ ውስጥ ዋነኛው ክፍል ነው፡፣ ትኩረቱና ጥረቱ በአጠቃላይ በሚሰራው የጥበብ ስራ ላይ እንጂ በቁስ ነገር-[ማቲሪያሊስቲክ] ያለመሆኑ ሌላኛው የፍቅር ሃይል በልጁ ውስጥ ተደላድሎ እንዲቀመጥበትና እንዲጠቀምበት ያስቻለ የልጁ ተፈላጊ ስነ-ባህሪይ ነው።

ብዙዎች ውጤታማ አርቲስትነታቸውን በተለይም ግጥሙንም ሆነ ዜማውን እራሳቸው እየደረሱ ለተከታታይ ዓመታት ከብቃት መዋዠቅ ይልቅ ይበልጥ የፈጠራ ክህሎታቸው የመጨመርን ተግባር ሲፈጽሙ ለማየት አዳጋች በሆነበት የስራ ጸባይ ልጁ-የፈጠራ ክህሎቱን ይበልጥ እያጎለበተና እያሻሻለ የመገኘቱ ምስጢር በጥበብ አማልእክቶች ዘንድ እጅግ  ተፈላጊና ተመራጭ የሆኑትን ቸርነት፣በጎነት፣ፍቅር፣እምነት እና ጽናትን የተላበሰ ግለ-ስብእናን በመጎናጸፉ ነው። ጥበብን ስታከብራት፣ፍቅርን መቻቻልን፣ውበትን እና አድናቆትን ስትገልጽባት ይበልጥ በጥበብ ላይ ጥበብን እና ማስተዋልን ጨምራ ትሰጥሃለች። አክብረሃታልና እሳም በጥበቡ ዓለም አንግሳ ታከብርሃለች -ታስከብርሃለችም። ቴዲ አፍሮ በህወሃታውያን ዘንድ ጥርስ ውስጥ ያስገባውን እና ለጨለማው ሃይል ተሸካሚ ሃይሎች ጥቃት ያጋለጠውን “ጃ-ያስተሰርያልን” ስራ ብንመለከት እንካን-እውነትን ይናገርና ሆኖም በይቅርታና በምህረት አስፈላጊውን አገራዊ አንድነት እንፈጥር ዘንድ የሚማጸን ሃያል የፍቅርና የይቅር ባይነት መንፈስ ያለው መሆኑን እናያለን። ኢትዮጵያዊ አንድነትን፣ይቅር መባባልን እና የተፈጠረውን ታሪካዊ ኩነቶችን በእውነትነት መቀበል እማይሻው ህወሃት መራሹ ስርዓት ግን የተጠናወተው መንፈስ ከእውነትና ክፍቅር መንፈስ ጋር የተጣላ የጨላማው መንፈስ በመሆኑ ልጁን ለመጉዳትና ለማጥቃት እንዳበቃቸው እንረዳለን እንጂ ቴዲ አፍሮ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ለመጥፎ ብጥብጥ የሚያነሳሳ ቀስቃሽ ስራ ሰርቶ እንዳልሆነ እምናየው እውነታ ነው።

3ኛ)ከአምስተኛው ከፍታ የተሰጠው ሃላፊነት እና ተልእኮ-

ሃላፊነትና ተልእኮ አልባ የንግስና ቅባት ለማንም አይሰጥም -በተሪካም ተሰጥቶ አያውቅም። “ኢትዮጵያዊነትን ማዳን” ከዚህ ቀጥሎ የስራው ዋና ተልእኮና ዓላማ መሆኑን በ40ኛ ዓመቱ ላይ ያለው ልጅ ቴዲ አፍሮ በአንደበቱ ይፋ አድርጋል። ኢትዮጵያዊነት አደጋ ላይ ነው። ኢትዮጵያዊነት በከፍተኛ ጥቃት ስር ያለ የቆሰለ እና የታመመ መንፈስና አካል ነው። የታመመው ኢትዮጵያዊነት መዳን ይኖርበታል። ፈዋሽ መድሃኒቱም በፍቅር ሃይል እሚመራው እራሱ የኢትዮጵያዊነት ሃያል መንፈስ መልሶ በማንሰራራትና የኢትዮጵያን አይርና ግዛት፣ህዝባን እና መልክዓ ምድራን ሲቆጣጠር ነው። ይህ ክስተት እውን ይሆን ዘንድም የኢትዮጵያዊነት ህያው መንፈስ በቴዲ አፍሮ ፍላጎትና ምርጫ ብቻ ሳይሆን በራሱ የኢትዮጵያዊነት ሃያል መንፈስና የፍቅር ሃይል መራጭነት ቴዲ አፍሮ ተመርጦ መገለጫ ሆናል። ቴዲ አፍሮ ብቻውን አይደለም – ለአሸናፊው ኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተገዙ እና ለኢትዮጵያዊ አንድነት ህልውና መጽናት ውድ ህይወታቸውንም ጭምር በደስታና በፍቅር መስዋእት አድርገው እውን ለማድረግ የቆረጡና የሚሹ እኔን ጨምሮ በሚሊዮንስ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነገድ አሉ-ከቴዲ አፍሮ ሃላም ተሰልፈው ይገኛሉ። ከሁሉ በላይ ግን የሃያሉ ኢትዮጵያዊነት ሃይልና ቃልኪዳን የገባላት አምላክ ከቴዲ አፍሮና ከተሰጠው ተልእኮ ጋር ያለ የመሆኑ እውነታ ነው።

“በአደጋ ላይ የወደቀውን ኢትዮጵያዊነትን የማዳን ተልእኮ ይዞ ነው ይህ ኢትዮጵያ የተሰኘው አልበም ለመሰራት የበቃው” እሚለን ልጅ ቴዲ አፍሮ የተሰጠውን ተልእኮና ሃላፊነትን ለመወጣት በፍጹም እምነት እና ቆራጥነት ተቀብሎት የተነሳ ልጅ ሆናል። ቴዲ አፍሮ ቆርጣል። እንደ የዚህ ትውልድ የሕዝብ ድምጽነቱ ማድረግ ያለበትን ለማድረግ ቆርጦ ተነስታል።ይህንን ውሳኔውን በታላቅ አድናቆትና ፍቅር ተርድቼያለሁ።እንደ ኢትዮጵያዊነቴም በቴዲ አገራዊ ተልእኮ ውስጥ የራሴን ግላዊ ድርሻና ሚናን በሚገባ ተረድቼ የበኩሌን ተሳትፎና አስተዋጽኦ አናሳ ነው በሚል ምዘና ሳላቃልልና ሳላጣጥል ማድረግ ያለብኝን ለማድረግ በፍቅር ሃይልና በኢትዮጵያዊነት ሃያል መንፈስ አዛዥነት የታዘዝኩትን በጸጋ ተቀብያለሁ። አንተም -አንቺም -ሁላችንም በኢትዮጵያዊነት የምናምን እና በኢትዮጵያዊ አንድነት የምናምን የዚህ ትውልድ አባላት በሙሉ- ኢትዮጵያ ሆንን አሜሪካ – ካናዳ ሆንን አውሮፓ- አረብ አገር ሆንን በአፍሪካ አንድ መንፈስ ያለን ትውልድ ነን። ይህንን አምናለሁ። ቴዲ አፍሮ ይህንን ታላቅ መንፈስና ታላቅ ተልእኮ ተቀብሎ እየተገበረ ያለ የኢትዮጵያዊነት፣ የኢትዮጵያዊ አንድነትና የሃያሉ ፍቅር አማኛ እና መገለጫ የዘመናችን ክስተት ሆናል።ይህ የእሱ ምርጫ አይደለም። የመራጩ ህይልና መንፈስ ምርጫ እንጂ። እኔና እናንተም ይህን መንፈስ የምንጋራና የምናምንበት ኢትዮጵያውያን ነን።

   የኢትዮጵያዊነት ሃያል መንፈስ በታላቅ ታሪካዊ ስራና እንቅስቃሴ ላይ ስለመሆኑ ብዙ ተግባራትን እያየን ነው። ባለፈው ዓመት በዚሁ ተመሳሳይ ወራት የ5ሺህ ዘመን ታላቁን የኢትዮጵያዊነትን ታሪክ ከዚህ በፊት ባልቀረበ መልኩ በድንቅ አቀራረብ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” መጽሃፍ ለንባብ ቀርቦ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለበትን ክስተትም በዚህ አጋጣሚ ለመጥቀስም እወዳለሁ። የፕ/ሩ ስራ ሃያሉን የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ በድንቅ አገላለጽና አቀራረብ ከ5ሺህ ዘመን ጀምሮ ያለውን ታሪካችንን በመተረክ ለኢትዮጵያዊነት መንፈስ ዳግም ማንሰራራት ታላቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ ድንቅ ስራ ነው።

  ቴዲ አፍሮ ዛሬ ይህንን ሃያል ሃይልና መንፈስ በሚደንቅ አገላለጽና አስተነጋገድ እየገለጸው ያለ ልጅ ሆናል። አዎን- ቴዲሻ ከቶም ብቻውን አይደለም- ከሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ሌላ አሸናፊውና ሃያሉ ኢትዮጵያዊነት መንፈስና የፍቅር ሃይል ከሃላው ያደረገ ክስተት ነው።

ሁላችንም ለተግባር እንነሳሳ-ድርሻችንንም እንወጣ።ኢትዮጵያዊነት ሃያል ነው። አሸናፊም ነው-ቴዲ አፍሮ በአምሰተኛው ከፍታ ላይ የተሰጠውን የኢትዮጵያዊነትን እና አገራዊ አንድነትን መልሶ የመጠገን እና ብሎም አጠናክሮ ሃያል ማድረግ ስራና ሃላፊነት በእያንዳንዳችን ትክሻ ላይ ያረፈ የወቅቱ ግን የዛሬና የነገ ህልውናችን ስራ ነው። ከዚህ የበለጠስ ስራ ምንስ አለ?