የአናሳው ቡድን ሕወሃትና በውስጡ እያደገ የመጣው የአመራርና የቅቡልነት ቀውስ ( ከነጻነት ቡልቶ)

0

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የሕወሃት ሊቀመንበር የነበሩት አቶ መለሰ ዜናዊ ከሞቱ በኋላ ተቀባይነት አግኝቶ ድርጅቱን በእሱ ዓይነት ተክለ-ሰውነትም ሆነ የተካነ ሴረኝነት ሊመራው የሚችል ሰው እስካሁን አልተገኘም። ይህ ክፍተት ድርጅቱን እያደገና እየጎለበተ ለመጣ ውስጣዊ ክፍፍልና ስር የሰደደ የእርስ በርስ ጥላቻ እንዳጋለጠው መረጃዎች ይጠቁማሉ። የወቅቱ የትግራይ ክልል አስተዳዳሪና የሕወሃት ሊቀመንበር የሆነው አቶ አባይ ወልዱ የስልጣኑን ሙሉ ኃይል በመጠቀምም ይሁን የጓዶቹን አክብሮትና ትኩረት በማግኘት ረገድ የመለሰ ዜናዊን ያክል ትንሽም እንኳን አልተሳካለትም። በመሆኑም በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረው የጠንካራ መሪ እጦት የተነሳ በአመራሮቹ መካከል ከፍተኛ የሆነ የስልጣን ሽኩቻ ተከስቷል። ይህንን የታፈነ እውነት የሚያጋልጡ ታማኝ የውስጥ ምንጮችም ከተለያዩ አቅጣጫዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።

ከሁሉም የከፋ ልዩነትና የመከፋፈል አደጋ ያንዣበበው በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና በወታደራዊ መረጃ መካከል ነው። በኢሕአዴግ ፓርቲ ፣ በስለላና ደህንነት ተቋማት፣ በመከላለከያና በቢሮክራሲው መካከልም ተመሳሳይ የሆኑ ሽኩቻዎች እያደጉ መጥተዋል። በግልጽም ሆነ በሚስጥር የሚሾልኩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ስርአቱን የሚያሽከረክሩ ጥቂት ግለሰቦች በቀጥታ እየተሳተፉበት ያለ ውስጣዊ ጦርነትም በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ እየተጧጧፈ በመካሄድ ላይ ነው።

በአንድ በኩል ለኢሕአዴግ ታማኝ በመሆንና በሌላ በኩል ደግሞ በመላ አገሪቱ በተቀጣጠለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት መካከል የትኛውን መንገድ መከተል አቅቷቸው እያመነቱ ካሉ አጋር ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ኦሕዴድና አባላቱ ለሶስት አስርት ዓመታት ተይዞ የነበረውን የሕወሃት የበላይነት በግልጽ መገዳደርና አንገታቸውን ቀና ቀና ማድረግ ጀምረዋል። ይህንን ያበጠ የኦሕዴድ ጡንቻ ለማስተንፈስ በመላው ኦሮሚያ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ የድርጅቱን ህልውና ከማናጋቱና የአባላቱን አንድነት አደጋ ላይ ከመጣሉ በፊት ከተወሰዱት እርምጃዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው በዝቅተኛና መካከለኛ አመራር እርከን ላይ የነበሩትን ብዛት ያላቸው የድርጅቱን አባላት ከስራ ማባበርና በምትካቸው አዲስ አመራሮችን ማስገባት ነበር። እነኚህ አዲስ የተመለመሉ አመራሮችም ቢሆኑ ቀስ በቀስ ከስራቸው እየለቀቁ መሆኑን የውስጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የዘረኛው የሕወሃት ስርአት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁንም ሆነ ይህንን አዋጅ በስራ ለመተርጎም ያቋቋመውን የ“ኮማንድ ፖስት” አፋኝ መሳሪያ የሚቃወሙ ድምጾች በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች እየተሰሙ ነው። ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎችና ማህበራዊ አጋጣሚዎችም ላይ ጎልቶ የሚሰማው ይኸው የተቃውሞ መንፈስ ሆኗል።

ዳግመኛ የተቀሰቀሰውን የኦሮሞ ሕዝብ ተቃውሞ ተከትሎ ኦሕዴድ የገባበትን ከፍተኛ የሆነ ውጥረት ለማርገብ የኢህአዴግ ፓርላማ አፈ ጉባኤና የድርጅቱ የቀድሞ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ አባ ዱላ ገመዳ ደፋ ቀና ማለት ጀምረዋል። እንደሚታወቀው አቶ አባዱላ ገመዳ የመከላከያው ኤታ ማጆር ሹም ከሆነውና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በበላይነት ከሚመራው ከጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው። የኮማንድ ፖስቱ ከፍተኛ የአመራር ስልጣን ለሳሞራ ዩኑስ መሰጠቱ ደግሞ ለአንዳንድ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የሚዋጥላቸው አልነበረም። በተለይም ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሰሜን እዝ አዛዥ ለነበረውና የወቅቱ የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ሃላፊ ለሆነው ለሌተናል ጄኔራል ሳዕረ መኮንን መራራ ኪኒን ሆኖ ቆይቷል።

የሳሞራ ዩኑስ ታማኝ  የሆነው ሌተናል ጄኔራል አብርሃ ወልደማሪያም ወይንም በቅጽል ስሙ “ኳርተር” በመከላከያ ውስጥ የህብረት ዘመቻ ዋና ሃላፊ ሆኖ ተሹሟል። ይህ ጄኔራል የደቡብ ምስራቅ ዕዝ አዛዥ በነበረበት ጊዜ የኦጋዴን ክልል አስተዳዳሪ ከነበረው ግለሰብ ጋር በመተባባር በአሸባሪነት ስም በግልጽና በድብቅ የብዙ ሺህ ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት በግፍ የጨፈጨፈና በዘር ማጥፋት ወንጀልም የሚፈለግ ግለሰብ መሆኑ ይታወሳል። ያም ሆነ ይህ ሳሞራ የኑስ ማንም የማይነቀንቀው ሰው መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቶአል። እናም የሳሞራ የኑስም ሆነ የአብርሃ ወልደማሪያም አይነቶቹ ከፍተኛውን የስልጣን ኮርቻ መቆናጠጥ  በግልጽ የሚያሳየው ሳዕረ ሞኮንን  ሆን ተብሎ ከጨዋታው የተገፋ ሰው መሆኑን ነው። በዚህ የጄኔራሉ መገፋት ያልተደሰቱ እንደ ደህንነቱ ዋና ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ አባይ ፀሃዬ፣ አቦይ ስብሃት ነጋ ፣ የቀድሞው የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) እና ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጀኔራል ሳሞራ የኑስን ከስልጣኑ አስወግደው በምትኩ ሳዕረ መኮንንን ለማስቀመጥ ውስጥ ውስጡን ከፍተኛ መሯሯጥ እያደረጉ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እንደሚታወቀው ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖትና አንድ ቅርብ ወዳጃቸው የቀድሞ  ኤታ ማጆር ሹሙ ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይ ህወሃት/ኢሕአዴግ እየተከተለ ያለውን መንገድና አጠቃላይ በስርአቱ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን በአደባባይ ግልጽ አውጥተው መተቸታቸው ይታወሳል። በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ባለፈው ዓመትና በድጋሚም  ከጥቂት ሳምንታት በፊት  ተደጋግመው በወጡ ጽሁፎቻቸው ላይ እንዳሳሰበው የሕወሃት/ኢሕአዴግ መንግስት የሀገሪቱን ደህንነትና ሕልውና አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እየከተተ እንዳለና ይህ ሁኔታ ባስቸኳይ እልባት ካልተገኘለት ሀገሪቱ እንደሀገር የመቀጠል ዕድሏ አሳሳቢ እየሆነ የመጣ መሆኑን፡ የብሄራዊ ደህንነት ኣደጋ ኢትዮጵያ መጋለጡዋን፣ የብሄር ግጭቶችም ሊነሱ እንደሚችሉ በጽሁፋ አጽንዖት የሰጠው ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል። ሌተናል ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት በመጨረሻ ላይ ባወጣው ጽሁፉ ከፍተኛ የመንግስት ሹማምንቶችን ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገና እየተንሰራፋ የመጣው የሙስና ችግር፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የዲሞክራሲ ምህዳር መጥበብ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ ፣ ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ያለመስጠት ችግርና እነዚህን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች በብቃት ለማለፍ መንግስት ያሳየው የአዕምሮ ብቃት ማነስ፣ የፖለቲካ ፈቃደኝነትና ድፍረት አለመኖርና የህዝቡን ብሶትና ቁጣ የሚያባብሱ የግድያ፣ የአፈናና የእስራት እርምጃዎችን መውሰዱን ክፉኛ አብጠልጥሎታል።

ጡረተኛው ጄኔራል ሲቀጥልም ኢትዮጲያ እነኚህን የተጋረጡባትን ችግሮች በጊዜ መፍታት ካልቻለች እነኚህ ችግሮች ውስጥ ውስጡን አድገውና ስር ሰደው ባልታሰበ ጊዜና ቦታ ፈንድተው የሃገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ ይጥላሉ ብሏል። ይህን የጡረተኛው ጄኔራሉን የማንቂያ ደወል ልብ ብሎ የሰማው ኃይል ግን ያለ አይመስልም። ምንም እንኳን አቶ አበበ ተ/ሃይማኖት የኢትዮጲያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ያነሳቸው ነጥቦች ትክክለኛ ስዕሉን ቢሰጡም ለነኚህ ችግሮች መልስ ይሆናሉ ብሎ የሰጣቸው ሃሳቦች ግን ፈጽሞ የተሳሳቱና ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው። ኢትዮጵያ ለተጋረጡባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሄ መሆን የሚችለው ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ሲቋቋምና ሀገሪቱ በሕዝብ በተመረጠ መሪና ዲሞክራሲያዊ ስርኣት ስትተዳደር ብቻ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል።

በአሁን ሰአት ካሉት ቁልፍ የኦህዴድ አመራሮች መካከል አቶ ለማ መገርሳ ፣ በከር ሻሌ ( እስከ ቅርብ ጊዜ) እና የቀድሞው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የነበረውና በኣደባባይ እምብዛም የማይታየው አቶ አብይ መሃመድ ይገኙበታል። እነኚህ ሶስቱ የኦህዴድ ባለስልጣናት ልክ እንደ አለቃቸው እንደ አቶ አባዱላ ገመዳ ከሳሞራ የኑስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ሲኖራቸው ከደህንነት ሃላፊው ከጌታቸው አሰፋ ጋርም አይጣጣሙም። ጌታቸው አሰፋ በበኩሉ በተለይም የኦሮሞ ህዝብ አመጽን ተከትሎ ለወሰዳቸው እርምጃዎች የአቶ አባይ ጸሃዬና የአቦይ ስብሃት ነጋ ትልቅ ድጋፍ እንዳለው ታውቋል። በአንድ ወቅት የደህንነት ሹም የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ ለአቶ አባ ዱላ ገመዳ ያለው ታማኝነት እጅግ ጥብቅ ሲሆን አቶ አባዱላም ይህንን ውለታ ለማካካስ አቶ ለማ መገርሳን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት እንዲሆን ረድቶታል። በደህንነት ቢሮውና በኦህዴድ ባለስልጣናት መካከል ያለው የስር በርስ ጥርጣሬና አለመተማመን ከፍተኛ ቢሆንም አቶ ለማ መገርሳ ግን እስካሁን ድረስ ከጌታቸው አሰፋ ጋር ያለውን የቀን በቀን ግንኙነት ለአቶ አባዱላ ገመዳ እያጠናቀረ እንደሚያቀርብለት ምንጮች ይጠቁማሉ።

አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ግን በዚህ ሁሉ የፖለቲካ ስልጣን ሽኩቻና ማለቂያ የሌለው በሚመስለው የህወሃት ፍትጊያ ውስጥ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሲያደርግ አይታይም። ተመልካች እንጂ ተዋናይ አይመስልም። ሆኖም ግን ከሳሞራ የኑስ ጋር የበለጠ ቅርበት እንዳለው ይነገራል። በዚህ ቅርበቱም የተነሳ ሳይሆን አይቀርም በቅርቡ የመንግስት ሚኒስትሮችና ሃላፊዎችን የወረደ የብቃት ደረጃ አስመልክቶ አባይ ፀሃዬ ላቀረበው ትችት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይህን ሪፖርት እኛ አናውቀውም” በሚል በልበ ሙሉነት የተቃውሞ ምላሽ ሊሰጥ የቻለው።

እነኚህ አቶ አባይ ጸሃዬ በብቃት ማነስ ያብጠለጠላቸው የመንግስት ሃላፊዎች የተሾሙት የአስቸኳይ አዋጁን ተከትሎ “ጥልቅ ተሃድሶ” በተባለው አሰራር መልካም አስተዳደርን ለማምጣት ፣ ሙስናን ለመዋጋትና የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ይችላሉ ብለው አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ያመኑባቸው ባለስልጣናት ነበሩ። በእርግጥም እነኚህ ሰዎች በዚህ ብዙ በተወራለት የጥልቅ ተሃድሶ አሰራር በአማራና በኦሮሚያ ክልል ለተነሱት ግብታዊ አመጾች ተግባራዊና አዎንታዊ  ምላሽ የመስጠት ምሁራዊም ሆነ መንፈሳዊ ብቃት እንደሌላቸው በግልጽ አስመስክረዋል። ይልቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ጥልቅ ተሃድሶ የተባለ ባዶ ወሬ ስርዓቱ የህዝቡን ድምጽና ብሶት ለማዳፈንና አቅጣጫ ለማስቀየስ የተጠቀመበት የማጭበርበሪያ ዘዴ እንጂ ሌላ ሊሆን እንደማይችል ተገንዝቦታል።

የኢሕአዴግ አንድ አካል የሆነው የብአዴን አመራሮችም ቢሆኑ ከሕወሃት ጋር አይንና ናጫ ከሆኑ ሰነባብተዋል። ግልጽ ቅራኔዎችም አደባባይ እየወጡ ነው። እንደ ኦህዴዶች ሁሉ የባህርዳሩንና የጎንደሩን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ሕወሃት በዋናነት የመራውና የወሰደው ዘግናኝ እርምጃ በብአዴኖች ላይ ያሳደረባቸው ቁጭትና ምሬት ቀላል አይደለም። የሕወሃት የበላይነት እስከመቼ ድረስ? የሚለው ጥያቄ እየጎላ መጥቷል።

ሕወሃት የሚቆጣጠረው መከላከያም ቢሆን በዘቀጠ ሞራል ውስጥ እንደሚገኝ ታውቋል። በተለይም ደግሞ መሳሪያ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የነጻነት ታጋዬች በሚገኙበት አካባቢ ማንም የስርዓቱ ወታደር መዋጋት እንደማይፈልግና ከመከላከያ ሰራዊቱም እየጠፉና እየከዱ የሚሄዱ የአማራና የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ወታደሮች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በመቶና በሻምበል ደረጃ ሙሉ አባላቱ ከነመሳሪያቸው መጥፋታቸው ከዚህ በፊት የታየ ሲሆን በተለይም ደግሞ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ጀምሮ በጨካኝነቱና አውሬነቱ የሚታወቀውን የአጋዚን ክፍለ ጦር እየከዱ የሚሄዱ አባላት ቁጥር በአሁን ሰአት እያደገ መጥቷል። ይህ ሁኔታ በተለይም ከኦሮሚያና ከአማራ ክልል አመጾች በኋላ እየተባባሰ መቷል። በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተወሰነ መልኩ በሌሎች ክልሎችም ውስጥ ውትድርናን የሚቀላቀል አዲስ ምልምል ተመዝጋቢ ጠፍቷል። ይህ ሁኔታ በኢሳትና በሌሎች መገናኛ ብዙሃን በሰፊው ሽፋን ተሰጥቶት የተዘገበ ጉዳይ ሆኖ አልፏል።

ሌላው ለሕወሃቶች ራስ ምታት የሆነው ችግር በሰሜን ኢትዮጲያ በኩል እየተቃጣባቸው ያለው ዉጊያ ነው። ይህን በኤርትራ መንግስት ይደገፋል የሚሉትን የነጻነት ትግል ለማዳፈን ብዙ የተለያዩ ሃሳቦችን እያንሸራሸሩ ነው። ከነዚህ ሃሳቦች ውስጥም ኤርትራን የመውረርና የተቃዋሚ ቤዞችን ማውደም አንድ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል። ሆኖም ግን ይህን አማራጭ ብዙዎቹ የመከላከያና የደህንነት መኮንኖች ተቃውመውታል። የወታደሩን ዝቅተኛ የመዋጋት ሞራልና ብቃት፣ የወታደሮች መክዳትና መጥፋት እንዲሁም በሰኔ 2016 ላይ በጾረናው ጦርነት የደረሰባቸውን ከፍተኛ ሽንፈት በማስታወስ ይህንን ኤርትራን የመውረር ጥያቄ ብዙም እንደ አማራጭ የሚወስዱት አይመስሉም። በተሳሳተ የጦርነት ስሌትና ውሳኔ የተገባበት የጾረናው ግጭት የመቀሌን ሆስፒታሎች በአስከሬንና በቁስለኛ ማጨናነቁን በጥልቅ ቁጭት በማስታወስ ይህ አይነቱ ስህተት አንዳይደገም ጥንቃቄ የወሰዱ ይመስላል። ይህ ብቻም አይደለም እነኚህን ጄኔራሎች ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ያገዳቸው ውስጣዊ ከፍተኛ ፍርሃትም አለባቸው። የመከላከያ መስሪያ ቤቱን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረውና የሚመራው ከአንድ ብሄር ብቻ የተውጣጣ ስብስብ መሆኑ በብዙ ኢትዮጲያዊያን ልብ ውስጥ ቅሬታን ፈጥሯል። በዚህም ላይ የተራው ተዋጊ ወታደር ሞራልና የመዋጋት ፍላጎት እጅግ በወረደ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። መከላከያውን በበላይነት የሚመሩት ጄኔራሎች በሚያስደነግጥ ደረጃ በሙስና የተዘፈቁ አዛዦች ስለመሆናቸው፣ የሞራል ብቃቱ እንደሌላቸውም ሰራዊቱ በደንብ የሚያውቀው ጉዳይ ነው። ይህ በመሆኑም የህወሃት ጄኔራሎች የደረሱበት ድምዳሜ አሁን ባለበት ሁኔታ በራሳቸው እዝ ስር የሚገኘውን የመከላከያ ሰራዊት ተማምኖ ወደ ጦርነት መግባት ማለት አመቺ መልክአ ምድር ይዞ ለሚከላከለውና ብቃትና ጥንካሬም ላለው የኤርትራ ጦር ለከፍተኛ ሽንፈትና ውርደት ራስን መዳረግ መሆኑን ነው ።

የብሄራዊ ደህንነትና ጸጥታ ሃላፊው ጌታቸው አሰፋም በበኩሉ የራሱን መስሪያ ቤት አቅምና ጉልበት ለማጠንከር ከፍተኛ ሩጫ ላይ ነው። በተለይም የሳሞራ የኑስ የቅርብ ደጋፊ ከሆነው የወታደራዊ መረጃ ክፍል ሃላፊው ከሜጀር ጄኔራል ገብሬ ዲላ በኩል የሚሰነዘርበትን የትችትና የንቀት ዱላ ለመከላከል እየባዘነ እንደሚገኝ ምንጮች ይጠቁማሉ። በመከላከያ ስር የሚገኘው የወታደራዊ መረጃ ክፍል ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ የስለላና የመረጃ ስራዎችን ከትላልቅ እስከ ትንንሽ የሃገሪቷ ክፍሎች ፣ መንደሮች ፣ ቀበሌዎች ፣ የአምልኮ ቦታዎችና የመሳሰሉት ድረስ ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆኑ ለረዥም ጊዜ በጌታቸው አሰፋ ቁጥጥር ስር የነበሩ ቦታዎችን የሚያስለቅቀው አዲስ ክስተት መሆኑ ጌታቸውን እንቅልፍ እንደነሳው ተዘግቧል።

በዚህ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤትና በመከላከያው ስር በሚገኘው የወታደራዊ መረጃ ክፍል መካከል የተነሳውን ልዩነትና ቅራኔ ተከትሎም በቅርቡ በህወሃት ባለስልጣናት መካከል ከፍተኛ የሆነ ውስጣዊ ሽኩቻና መጠላለፎች መበርከታቸው ታውቋል። በቅርቡ በስራ የዋለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከለላ በማድረግ ሳሞራ የኑስና ገብሬ ዲላ ከሚገባቸው በላይ የስልጣን ክልላቸውን በማስፋት ቀድሞ በጌታቸው አሰፋ ሰዎች ይሰራ የነበረውን የደህንነትና መረጃ ስራ እየነጠቁት ነው በሚል ይከሷቸዋል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ይህ ቅጥ ያጣ ፉክክር የዘረኛው የህወሃት ቡድን እርስ በርሱ በጥላቻ ፣ በመናናቅና በወገንተኝነት ስሜት እየመረዘ ወደ ለየለት የመከፋፈል አደጋ ሊወስደው ይችላል ይላሉ።

እነኚህ ሁሉ ይፋ የሆኑና ያልሆኑ የስልጣን ሽኩቻዎችና አንዱ አንዱን ለመደፍጠጥ  እየተጠላለፉ ባለበት ሰአት ላይ በተለይ በሰራዊቱ ውስጥ የሚታየው የሞራል ውድቀት ጌታቸው አሰፋ በሚመራው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ ዘልቆ እንደገባ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የመረጃ ምንጮች እንደሚጠቁሙት ለዚህ የደህንነት ሰራተኞች የወደቀ ሞራልና መዝረክረክ ዋናው ማሳያ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ላለፉት ሁለት አመታት የተቀጣጠለውን ህዝባዊ አመጽ አስቀድሞ መከላከል ይቅርና አመጹ ከተነሳም በኋላ መቆጣጠር አለመቻላቸው ነበር። የደህንነት መስሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁን ሰዓት ያለበትን አጠቃላይ የፖለቲካ ንቃት ፣ ለስርዓቱ ያለውን ጥላቻና ብሶት ለመረዳት የማይችልበት የበሰበሰና ኋላ ቀር አሰራር መቀየር አለመቻሉ ከጊዜው ጋር ማዝገምና መለወጥ ያልቻለ የደካማዎች ስብስብ አስመስሎታል። በሌላ በኩልም የአርበኞች ግንቦት 7 የነጻነት ታጋዮች በተለይ በጎንደርና አካባቢው ላይ በሚገኙ የስርአቱ የወታደራዊ ፣ የንግድ፡ የኣስተዳደርና  የደህንነት ተቋማት ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከጊዜ ወደጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱ የሕወሃት/ኢህአዴግ ባለስልጣናትን ከፍተኛ የሆነ ጭንቀትና ሽብር ውስጥ እንደጣላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።