ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ በካታር

  አባይ ሚዲያ ዜና
  አቢሰሎም ፍሰሃ

  ከ2011 ጀምሮ የአረብ አገራትን ሲከፋፍል እና ሲያናውጥ የነበረው የአረብ ስፕሪንግ አሁን ደግሞ የአረብ ገልፍ ሃገራትን ለሁለት ከፍሏቸዋል።

  ሳውድ አረቢያ፣ዩናይቲድ አራብ ኤሚራት፣ባሕሪን፣ግብጽ እና የመን በአንድ ጎራ ሆነው በትንሿ የአረብ አገር ካታር ላይ የተለያየ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል።

  ዛሬ ሰኞ 5/6/2017 ዩናይቲድ አራብ ኤሚሬት ማንኛውም የካታርን ሰንደቅ አላማ የሚያውለበልብ መርከብም ሆነ መድረሻውን ካታር ያደረገ ወደቤን መጠቀም አይችልም ብላለች።

  ግብጽ በበኩሏ በካይሮ ለሚገኘው የካታር አምባሳደር አገሯን ለቆ እንዲወጣ 48 ሰዓት መስጠቷን የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቁአል። በተመሳሳይ ካታር ዶሃ የሚገኙትን ልዑካኗን በሁለት ቀን ውስጥ ሙሉ በሙሉ ካታርን ለቀው እንዲመለሱ ትዕዛዝ ተላልፏል ብለዋል።

  ሳውዲ አረቢያ አላሳልፍም ያለቻቸው መድረሻቸውን ካታር ያደረጉ ምግብ የጫኑ በርካታ የጭነት መኪናዎች በድንበር ላይ ተሰልፈው መቆማቸውም ተገልጹአል።

  ይህ በእንዲህ እንዳለ መቀመጫውን ዩናይቲድ አራብ ኤሚራት ያደረገው ኤር አረቢያ ወደ ካታር የሚያደርገውን በረራ ከማክሰኞ ጀምሮ ላልተወሰነ ግዜ እንደሚያቆም አስታውቋል።
  ዱባይ ኤር እና ሳውዲ አረብያ አየር መንገድም ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዳቸው ታውቋል።

  የዚህ ሁሉ መንስዔ ካታር አማፂ እና አሸባሪን ትረዳለች የሚል ሲሆን ካታር በበኩሏ ምንም አይነት ህጋዊ ማስረጃ በሌለበት እኛን መወንጀል ሉአላዊነታችንን መጣስ ነው ብላለች።