እስራኤል እና ሒዝቦላህ ሊዋጉ ነው፣ዛቻውና ፍጥጫው አይሏል

አባይ ሚዲያ ዜና
ወንድወሰን ተክሉ
እስራኤል ሊባኖስ ባለው ሒዝቦላህ ላይ ጦርነት ከከፈተች ጦርነቱ በመቶሺህ የሚቆጠሩ ጸረ-እስራኤል ተዋጊዎች የሚሳተፉበት ታላቅ ጦርነት ይሆናል ሲሉ የሒዝቦላህ መሪ ሼህ ሀሰን ነስሩላህ አስጠነቀቁ።

የእስራኤል አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሜ/ጄኔራል አሚር ኤሽል “በሰሜን በኩል ከሒዝቦላና አጋሮቹ ጋር ጦርነት ከተከፈተ እስራኤል ያላትን ማንኛውንም ወታደራዊ ሀይል በመጠቀም በሙሉ ሀይላ ጦርነቱን በፍጥነትና በአጭር ግዜ ውስጥ ለመፈጸም ትዘምታለች” ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ አይ24ዜና ሪፖርት የሺዓ እምነት ተከታይ የሆኑት የሒዝቦላህ መሪ ሼህ ሀሰን ነስሩላህ ዓርብ ሰኔ 24 ቀን 2017 ባስተላለፉት የቀጥታ ቴሌቪዥን ንግግራቸው “ከእስራኤል ጋር የምናደርገው መጪው ጦርነት ከሶሪያ፣የመን፣ኢራቅ፣ፓኪስታን እና አፍጋኒስታን በመቶሺህ የሚቆጠሩ ወደ ዘማቾች የሚሳተፉት ጦርነት ነው” ማለታቸውን ዘግቧል።

የእስራኤል መንግስት ለህልውናዪና ለደህንነቴ የሚያሰጋ የጦር መሳሪያ ክምችት በሒዝቦላህ እጅ መገኘቱን አረጋግጫለሁ በሚል ድምዳሜ ጦራን ለሊባኖስ ዘመቻ እያዘጋጀች እንዳለች ተገልጿል።

እንደ አይ24ኒውስ ዘገባ ሒዝቦላህ ከ100.000 በላይ የአጭርና የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሮኬቶች ባለቤት መሆን መቻሉን ጠቅሶ የእስራኤልን ወታደራዊ ዘመቻ ቁርጠኝነት በአየር ሃይላ ዋና አዛዥ በኩል መገለጹን ይዘግባል።

ከወራት በፊት የእስራኤል አየር ሃይል የሊባኖስን እና የሶሪያን አየር በመጣስ ከኢራን በኩል ለሒዝቦላ የተላከ የጦር መሳሪያ ክምችት አገኘሁ በሚል ድብደባ መፈጸማ አይዘነጋም።

እንደ የእስራኤሉ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ገለጻ-እስራኤል ጦርነቱ በተጀመረ ቅጽፈት ውስጥ እስከዛሬ ተጠቅማ እማታውቀውን ከፍተኛ ቦምብ እንደምትጥል የገለጹ ሲሆን ጦርነቱም በአይነት፣በስልትና በሚጠቀሙበት የመሳሪያ ዓይነት ልዩ መሆን በመግለጽ ለስጋት የዳረጋቸውን የሒዝቦላህን የጦር መሳሪያ ክምችትና የአጋሮቹንም ወታደራዊ ሀይል እንደምትደመስስ ነው የሚያስረዱት።

ሆኖም የዋዛ ያልሆኑት የሒዝቦላህ መሪ ሼህ ነሰረላህ-የባለፈው 2006 ጦርነት በሊባኖስ ምድር ውስጥ የተፈጸመ ሲሆን አሁን ግን የምናካሂደው ጦርነት በጽዮናዊታ እስራኤል ግዛትና ምድር ውስጥ ይሆናል ማለታቸው ተዘግቧል።

የሒዝቦላህ መሪ አክለውም “ዛሬ ሒዝቦላህ የእስራኤልን ግዛት በአጠቃላይ ኢላማው ውስጥ ያስገባ ሮኬቶች ባለቤት ነው” ማለታቸው ተደምጣል።

ወደ የሶሪያ ዓየር ክልል በመግባት የሒዝቦላህን ሀይል እንመታለን ያሉት የእስራኤሉ ዓየር ሃይል ዋና አዛዥ -“በአሁኑ ሰዓት በሶሪያ አየር ክልል ውስጥ የሩሲያ፣የአሜሪካን እና የአውሮፓ ሀገር ተዋጊ ጄቶች የሚሳተፉበት በመሆኑ ግጭት እንዳይፈጠር አስፈላጊውን ጥንቃቄ ከወዲሁ አድርገናል” ሲሉ ገልጸዋል።

እስራኤል እና ሒዝቦላህ በ2006 ለ34ቀናት ያህል በፈጀ ጦርነት በሊባኖስ በኩል ከ1600 በላይ ሰዎች [አብዛኛዎቹ ሲቪል] እና በእስራኤል በኩል ከመቶ የሚበልጥ ወታደሮች መገደላቸው ይታወቃል።

የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካዊ ቀውስና በተለይም በኢራቅ፣በሶሪያና በየመን ከፍተኛ ደም አፋሳሽ የእርሰ በርስ ጦርነት ገና ሳይበርድ በእስራኤልና በሒዝቦላህ መካከል ጦርነት መነሳቱ ግጭቱን ወደ አልተፈለገ ደረጃና አቅጣጫ ይመራዋል ሲሉ የክልሉን ፖለቲካ የሚከታተሉ ዲፕሎማቶች ይናገራሉ።

የሳኡዲ ዓረቢያ ከመቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ የጦር መሳሪያ ግዢ ማግስት በኳታር ላይ የወሰደችው አቋምና በኢራን ላይም የያዘችው የከረረ አቋም ክልሉን ወደ ሌላ የጦር መድረክነት መቀየሩ አይቀሬ ነው ሲሉ ዲፕሎማቶች ይናገራሉ።