የኬኒያ ፍርድ ቤት በምርጫ ጉዳይ የተቃዋሚዎችን ሀሳብ አጸደቀ

አባይ ሚዲያ ዜና
ወንድወሰን ተክሉ

የኬኒያ ፍርድ ቤት በሀገሪቱ ጥምር የተቃዋሚ ሀይሎች [ናሳ]የቀረበለትን የምርጫ ውጤትን የመግለጽ እርምጃን ተገቢ እና በህገ-መንግስቱ ውስጥ የታቀፈ ነው ሲል አጸደቀ።

እንደ የኬኒያ ተቃዋሚ ሀይሎች ጥምር ሀይል [ናሳ]ፍላጎት በመጪው ሀገር አቀፍ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤትን ቀደም ሲል ሲጠቀሙበት ከነበረው ውጤቱን በአንድ ማእከላዊ የምርጫ ጣቢያ ከመግለጽ በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ እንዲገለጽ የሚጠይቅ ሲሆን ጥያቄውንም በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የጁብሊ መንግስት አልቀበልም በማለቱ ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ እንደቻለ ይታወቃል።

ይህንን የተቃዋሚዎቹን አቤቱታ ተቀብሎ የመረመረው የሀገሪቱ ፍርድ ቤት በተቃዋሚዎች የቀረበው ጥያቄ ተገቢነትን ካረጋገጠ በሃላ የሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ በመጪው ምርጫ ውጤቱን በየምርጫ ጣቢያዎቹ እንዲገልጽ ሲል ውሳኔውን አስተላልፋል።

የሀገሪቱ የበላይ አቃቤ ህግ የሆኑት ፕ/ር ሙንጋይ መንግስት በውሳኔው ላይ ይግባኝ ሊጠይቅ እንደሚችል ከመግለጽ ያለፈ ለግዜው ሌላ ሀሳብ አለመናገራቸው ታውቃል።

ኬኒያ በመጪው ነሀሴ 8ቀን 2017 በምታካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ 5ኛ ፕሬዚዳንታን ጨምሮ 47 ገዢዎችን [ገቨርነርስ]ከመቶ በላይ ሴናተሮችን እና ከ200መቶ በላይ የፓርላማ አባላትን እንደምትመርጥ ሲጠበቅ በተቃዋሚዎች በኩል ተደጋግሞ የተገለጸውን የምርጫ ውጤትን የማጭበርበር ተግባር በተቻላቸው መጠን የሚቀንሱበትን እና የሚያስቀሩበትን ታክቲካዊ እስትራቴጂ ነድፈው በመተግበር ላይ ያሉባት ሀገር ነች።

በተቃዋሚው በኩል እንደመፍትሄነት ከተወሰዱት እርምጃዎች ውስጥ ሶስት መሰረታዊ የምርጭ ተግባሮችን ያካተተ ሲሆን የመጀመሪያው እርምጃ የ2013ቱን ምርጫ በበላይነት የመራውን የኬኒያ ምርጫ ቦርድ ኮሚሽን ፈርሶ አዲስ መቃቃም አለበት በማለት የተገበሩት ተግባር ሲሆን ሁለተኛውና ሶስተኛው በምርጫው እለት በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ የተቃዋሚዎቹ ተውካይ ከምርጫ ቦርድ ቆጣሪዎች ጋር እኩል ጎን ለጎን የተሰጠውን ድምጽ መቁጠርና ውጤቱንም እዚያ በየምርጫ ጣቢያው ማሳወቅ የሚሉት ይገኙባቸዋል።
ሶስቱም መሰረታዊ የምርጫ ደንብና ህግ የወቅቱ ገዢ ፓርቲ ጁብሊ አልቀበልም እያለ ቢያንገራግርም ተቃዋሚዎቹ ባደረጉት በአመጽ እና በፍርድ ቤት የታጀበ ትግል ሳይወድ በግድ እየተቀበለ ለመፈጸም የተገደደ ፓርቲ እንደሆነ እየታየ ነው።

በመጪው ነሀሴ ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት በስልጣን ላይ ያሉት ኡሁሩ ኬኒያታ እና ታዋቂው የተቃዋሚዎች ህብረት መሪ አቶ ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ ቢሆኑም ሌሎች ወደ 5ት የሚጠጉ በግል ተወዳዳሪዎችም ለመወዳደር እንደተዘጋጁ መግለጻቸው ይታወቃል።