የስምንት አመቷ ስደተኛ ልጅ ከዶናልድ ትራምፕ እኩል ታዋቂ ናት ተባለ

አባይ ሚዲያ ዜና
ወንድወሰን ተክሉ

የስምንት ዓመቷ ሶሪያዊቷ ስደተኛ ባና አልቤድ ከ45ኛው የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እኩል የኢንተንርኔቱ ዓለም ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ [ታዋቂ] መሆኗን ታይም ዘገበ።

ሶሪያዊቷ ባና አልቤድ የሶሪያ አሌፖ ከተማ በታህሳስ 2016 በአይ.ሲ፣ ስ፣ በአሜሪካን ደጋፊ የአሳድ ተቃዋሚዎች እና በሩሲያ ደጋፊ የአሳድ ጦር መካከል ከፍተኛ ፍልሚያ በሚካሄድበት ወቅት እሷ በትዊተር ገጿ “ከዓለም ጋር በቀጥታ መነጋገር” በሚል መሪ ቲዊቷ የነበረችበትን ሁኔታዎች በመግለጽ የምትታወቅ ሲሆን በአንድ ወቅት “እኔ አሁን ካለሁበት ሁኔታ አንጻር በህይወት ልኑር ወይ ልሙት የማውቀው ነገር የለም” በሚለውና መሰል ቲዊቶቿ ከመቶ ተከታይ ተነስቶ እስከ 350 ሺህ ተከታዮችን ወዲያው በማፍራት ታዋቂ ለመሆን እንደቻለች የታይም ዘገባ ይገልጻል።

ሶሪያዊቷ የ8 ዓመት ልጅ በማህበራዊ ድረገጾች ላይ ከፍተኛ ተሰሚነትን ከፈጠሩ የኢንተርኔቱ ዓለም 20 ታዋቂዎች ውስጥ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጋር በአቻ አንደኝነትን እንደተጋራች ከዘገባው መረዳት ተችሏል።

በተጽእኖ ፈጣሪነትና ተሰሚነት የአንደኝነቱን ስፍራ የያዙት ሌላው ታዋቂ ሰው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሲሆኑ ፕሬዚዳንቱ የትዊተር ገጻቸውን በመጠቀም ፖሊሲያቸውን በመግለጽ ወዳጅና ጠላቶቻቸውንም በማወደስና በማጥቃት ስለገለጹበት ቀደምት የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ያላገኙትን ታዋቂነትና ተሰሚነትን ፈጥረዋል ሲል ታይም መጽሄት ዘግቧል።

ፕሬዚዳንቱ ትዊት በሚያደርጉት ጉዳዮች ተደጋግሞ የዓለም አቀፉን መገናኛ ብዙሃን የፊት ሽፋን እና ሰበር ዜና ሽፋን ማግኘት መቻላቸውን ጠቅሶ በግድየለሽነት የሚለቃቸው ትዊቶች ብዙ ጊዜ አወዛጋቢና አከራካሪ ቢሆንም ተሰሚነትን እና ታዋቂነትን አግኝተውበታል ይላል የታይም ዘገባ።

ፕሬዚዳንቱ በማህበራዊ ድረገጾች ላይ ታዋቂነትን ካስገኘላቸው አጉራዘለል ቲዊቶቻቸው ውስጥ የተወሰኑትን ለናሙና ያህል ታይም ያወጣ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንዱ “..Sorry losers and haters, but my I.Q. is one of the highest – and you all know it! Please don’t feel so stupid or insecure, it’s not your fault…” የሚለው የፕሬዚዳንቱ ትዊት ይገኝበታል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በአወዛጋቢ፣ አስፈጋጊ፣ አስበርጋጊ እና አስገራሚ ቲዊቶቻቸው ታዋቂነትን እና ከፍተኛ ተከታዮችን እንዳፈሩ ተገልጾ የ8 ዓመቷ ሶሪያዊቷ ልጅ ግን ከእድሜዋ በላይ በምታደርጋቸው ድርጊቶችን የመግለጽ አቅሟ ነው ሲል ያብራራል። ሆኖም የልጅቷ ጉዳይ ከፍተኛ ጥርጥሬ ያላቸውን ሰዎችም እንደፈጠረ የሚገልጸው ታይም የቲዊተር ገጽ አስተናጋጅ አንዳንዴ በልጅቷ ገጽ እናትየዋ ሳትጠቀምበት እንዳልቀረች ይገልጻል።

ሶሪያዊቷ ባና አልቤድ በአሳድ መንግስትና ሩሲያ ጦር አጥቂነት አሌፖን ለመቆጣጠር በተካሄደው ጦርነት መጨረሻ ላይ ነፍሷ ተርፎ ወደ ቱርክ በመሰደድ ዛሬ በቱርክ የስደተኞች ካምፕ እንዳለች ገልጿል። ሆኖም በስደትም ሆና ያላረፈችው ልጅ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጸረ-6 የሙስሊም ሀገራት ህግ ሲያወጣ ለምን ሙስሊሞችን ታጠቃለህ ብላ እንደወረፈችውም አክሎ ዘግቧል።