ሩሲያውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ፕሬዚዳንት ፑቲንን ከስታሊን ቀጥሎ መረጡ

አባይ ሚዲያ ዜና
ወንድወሰን ተክሉ

የሁለተኛው ዓለም ጦርነት አሸናፊ እንደሆነ የሚነገርለት የሶቪየት ህብረቱ ጆሴፍ ስታሊን በተወዳጅነቱ አንደኛ ሲሆን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቦልሼቪክ አብዮት መሪው ቮላድሚር ኤሊች ሌኒን የሁለተኝነትን እና ሶስተኝነትን ስፍራ እንደያዙ የሩሲያ 24 ዜና ጣቢያ ገለጸ።

በሩሲያ ውስጥ በተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት በተቀረው ዓለም ዘንድ በጨካኝነቱና ጨፍጫፊነቱ ስሙ የሚጠራው ጆሴፍ ስታሊን በተወዳጅነቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቃት ባለው ተመራጭ መሪነት የ38% ሩሲያውያንን ድምጽ አግኝቶ አንደኛ ሲሆን የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሌላውን ዓለም አቀፍ መሪያቸውን ሌኒንን በልጦ በ34% በሁለተኛነት እንደመረጡት ተዘግቧል።

የዛሬዎቹ ሩሲያውያን በቭላድሚር ፑቲን በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቃት ያለው መሪነቱ ከፍተኛ እምነት ያላቸው መሆኑን ጠቅሶ ይህ አቋማቸው ግን ፑቲንን ከስታሊን ጋር በማወዳደር የአንደኝነት ደረጃን እንዲሰጡ እንዳላደረጋቸው አብራርቷል።

እንደዜና ዘገባው ከሆነ ከ1990 ወዲህ የጆሴፍ ስታሊን ተወዳጅነትና ተፈላጊነት እየጨመረ የመጣ ሲሆን በአንጻሩም በእሱ ላይ ትችት፣ ነቀፌታና ጥላቻ ሲገልጹ የነበሩ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እያሽቆለቆለ መጥቷል ሲል ሪፓርቱ ይገልጿል። ለስታሊን ተመራጭነት ትልቁ ምክንያት ሩሲያውያኑ በእሱ ዘመን ሀገራቸው በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የነበራትን ተሰሚነት እና ብሎም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚዝምን በጽኑ ተዋጊነቱ ብቃት እንደሆነ ይገልጻል።

ቭላድሚር ፑቲን በጆሴፍ ስታሊን ዱካ የሚሄዱና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የሆኑ የሩሲያውያኑ የእድሜ ልክ ተመራጭ መሆናቸውን ጠቅሶ ፕሬዚዳንቱ የሩሲያን የቀድሞ ክብርና ተሰሚነት ለመመለስ የሚያደርጉትን ፖለቲካዊ አመራር በአድናቆት እንደተቀበሉላቸው ያብራራል።

በቅድመ አያቱ የኢትዮጵያ ተወላጅ እንደሆነ የሚታወቀው ታዋቂው ሩሲያዊ የጥበብ ሰው አሌክሳንደር ፑሽኪንን ሩሲያውያን በ3ኛነት ደረጃ እንደመረጡት ተግለጿል።