የአሜሪካ ከፍተኛው ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራምፕን የሙስሊም ሀገራት እገዳ በከፊል እንዲተገበር ወሰነ

አባይ ሚዲያ ዜና
ወንድወሰን ተክሉ

የአሜሪካው ከፍተኛ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አወዛጋቢውን የዶናልድ ትራምፕ ጸረ-ስድስት ሙስሊም ሀገራት ቪዛ እገዳና የስደተኛ አለመቀበልን ህግ 9 ለዜሮ በሆነ ድምጽ እንዲተገበር ሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2017 በዋለው ችሎት መፍረዱ ተገለጸ።

ፕሬዚዳንቱ ውሳኔውን ተገቢና የሀገራችንን ደህንነት የሚያረጋግጥ ሲሉ አሞካሽተው እና ዳኞቹንም አድንቀው ተቀብለውታል።

ትራምፕ ዛሬ ለአሜሪካውያን ታላቅ ቀን ነው ሲሉ በቲዊታቸው እንዲህ በማለት “Great day for America’s future Security and Safety, courtesy of the U.S. Supreme Court. I will keep fighting for the American people, & WIN!” ደስታቸውን ገልጸዋል።

ክፍተኛው ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድቤቶች የታገደውን ይህን አወዛጋቢ የቪዛና የስደተኞች ህግ ሽሮ የፕሬዚዳንቱን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ ከፈረደ በኋላ በመጪው ህዳር በጉዳዩ ላይ የቀረበውን የአይተግበር አቤቱታ እንደሚመረምር ቀነ ቀጠሮ ሰጥቶ እስከዚያው ድረስ ከሃሙስ ሰኔ 29 ቀን 2017 ጀምሮ ከፕሬዚዳንቱ የወጣው ህግ ተግባራዊ እንዲሆን በአንድ ድምጽ ወስነናል ሲል ፍርዱን አሰምቷል።

በዚህ መሰረትም ከፊታችን ሀሙስ ሰኔ 29 ቀን ጀምሮ ከሊቢያ፣ ሶሪያ፣ ሶማሊያ፣ ኢራን፣ የመን እና ሱዳን የሚመጡ ዜጎች ወደ አሜሪካ የሚያስገባቸውን የመግቢያ ቪዛ እንዳይሰጣቸው ሲል የወሰነ ሲሆን ክፕሬዚዳንቱ ረቂቅ ህግ በተለየ ሆኖ የታየው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከተጠቀሱት ስድስት የሙስሊም ሀገራት ያሉ ዜጎች ልዮ ግንኙት በአሜሪካ ውስጥ ያላቸው ለምሳሌ በአሜሪካን ዩኒቨርስቲዎች የተመዘገቡ ተማሪዎች በአሜሪካን ግዛት ውስጥ በስራ ላይ ባሉ ሰዎች እና ከአሜሪካን ጋር በስጋ ዝምድና የተሳሰሩት ላይ ህጉ ተፈጻሚ አይሆንም ማለቱ ተዝግቧል።

ዲሞክራቶችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በውሳኔው ቅሬታቸውን ሲገልጹ ተሰምተዋል። “ጠቅላዩ ፍርድ ቤት ህገ-መንግስታችንን የሚጻረር ውሳኔ ነው ያስትላለፈው” ሲሉ ተናግረዋል።

የፕሬዚዳንት ትራምፕ አወዛጋቢው ህግ አጠቃላይ ስደተኛ ለ4 ወር ወደ አሜሪካን እንዳይገባ የሚያግድ ሲሆን ለተጠቀሱት ስድስት የሙስሊም ሀገራት ዜጎች አጠቃላይ የቪዛ ፍቃድን የሚያግድ እንደሆነ ይታወቃል።

ድኞቹን ውሳኔውን ለመስጠት ካስቻሏቸው ምክንያቶች ውስጥ በየጊዜው እያደገ የመጣው የአሸባሪዎች ጥቃት እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ ተንታኞች ደግሞ የሰሞኑ የአሸባሪዎች በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በፈረንሳይና በቤልጂየም የተስተዋለው ተደጋጋሚ ሙከራና ጥቃት ተጽእኖ ሳይፈጥርባቸው አልቀረም ይላሉ።