የህወሓት የማኅበራዊ ሚዲያ ካድሬዎች አዲስ ተልዕኮ ተሰጣቸው

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

ህወሓት/ኢህአዴግ የማኅበራዊ ሚዲያ ካድሬዎች አዲስ ተልዕኮ እንደተሰጣቸው ምንጮች ጠቆሙ። ተልዕኮው ከትላንት በስቲያ ይፋ የተደረገውን የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ግንኙነት የተመለከተውን ሰነድ የሚመለከት ሲሆን፣ ሰነዱ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ከሚገባው በላይ እንዲራገብ፣ ግራ እንዲያጋባ እና ብዥታ እንዲፈጥር መስራት እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል።

በተጫማሪም ሰነዱ፣ የኦሮሞ ህዝብ ለዓመታት ሲያቀርብ የነበረውን ጥያቄ እንደመለሰ በማድረግ፣ ትግል ላይ የሚገኘውን ህዝብ ለማደናገር ጥረት እንዲያደርጉ ታዘዋል፡፡

ለካድሬዎቹ ከላይ የወረደው ትዕዛዝ እንደሚያመላክተው ከሆነ፣ ሰሞነኛው የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ አዳዲስ ለውጦችን አድርጎ መጥቷል። በማኅበታዊ ሚዲያ ላይ የሚካሔደው የህወሓት ካድሬዎች የፕሮፓጋንዳ ጦርነት፣ የተቃዋሚ ሰዎችን ፎቶ ፕሮፋይል በማድረግ ጭምር እንዲካሔድ ተነግሯቸዋል። በዚህም መሰረት በተለይ ደግሞ በእስር ላይ የሚገኙትን ዶ/ር መረራ እና አቶ በቀለ ገርባን ፎቶ ፕሮፋይላቸው በማድረግ እና ተቃዋሚ በመምሰል፣ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያን ክልል ግንኙነት የተመለከተውን ሰነድ እንዲያሞካሹ ግዳጅ ተሰጥቷቸዋል። ይህም በትግል ላይ የሚገኘው የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄው እንደተመለሰ አድርጎ ለማራገብ ታስቦ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል።

በተቃዋሚዎች ፎቶ ስር ተወሽቆ ሰነዱን ከማንቆለጳጰስ በተጫማሪም፣ ከሰነዱ ላይ አወዛጋቢ የሆኑ አንቀጾችን በመምዘዝ የማደናገር እና ህወሓትን ለመታገል በተሰለፉ ወገኖች መካከል ያለውን የትግል ስሜት ጥርጣሬ ላይ ለመጣልም አዲስ ዘመቻ እንዲካሔድ ትዕዛዝ ተላልፏል። በሌላም በኩል፣ ኦሮምኛ በአዲስ አበባ የስራ ቋንቋ እንዲሆን እና ፊንፊኔ የሚለው ስያሜ አዲስ አበባ ከሚለው ስያሜ ጋር አብሮ መጠሪያ እንዲሆን መደረጉን የትግሉ ፍጻሜ አድርጎ መስበክም ሌላኛው የህወሓት ካድሬዎች የውንብድና ተልዕኮ መሆኑም ታውቋል፡፡

በዚህ ዓመት መጀመሪያ መስከረም ወር ላይ ለንባብ የበቃው እና የህወሓት/ኢህአዴግ አቋም የሚንጸባረቅበት ‹‹አዲስ ራዕይ›› መጽሔት በአቋም ደረጃ ካሰፈራቸው ጽሁፎቹ መካከል፣ የካድሬዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ አንዱ ነበር። መጽሔቱ፣ ኢህኤዴግ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተቃዋሚዎች የበላይነት እንደተወሰደበት የገለጸ ሲሆን፣ ይህን የበላይነት ለመቀልበስም አዳዲስ ካድሬዎችን አሰልጥኖ ማሰማራት ተገቢ መሆኑንም መጽሔቱ ገልጾ ነበር።

በከፍተኛ የህወሓት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት የሚዘጋጀው እና የሚጻፈው ይኸው መጽሔት፣ ካድሬዎች ከፌስ ቡክ በተጨማሪም በትዊተር፣ በዩቲዩብ እና በመሰል የመገናኛ ዘዴዎች የፕሮፓጋንዳ ስራ እንዲሰሩ መደረግ እንዳለበት ገልጾ ነበር። መጽሔቱ ለህትመት ከበቃ ከጥቂት ወራት በኋላ አዳዲስ ካድሬዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ውንብድና እንዲፈጽሙ የተሰማሩ ሲሆን፣ ለዚህ ‹‹ስራቸውም›› ደሞዝ ይቆረጥላቸዋል። ካድሬዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚያደርጉ ሰዎችን ስም አሳልፎ በመስጠት ብዙዎችን ሲያሳስሩ ቆይተዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን ተቃውሞ ተከትሎ፣ በኦሮሚያ ክልል ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን በአጋዚ ሲገደሉ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡ ሀገር ጥለው የተሰደዱትም በርካቶች ናቸው፡፡