አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ያላት ትእግስቷ ተሟጣል-ዶናልድ ትራምፕ

አባይ ሚዲያ ዜና
ወንድወሰን ተክሉ

አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ያላት ስልታዊ ትእግስት ተሟጣል ሲሉ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የገለጹ ሲሆን፣ አያይዘውም ከእንግዲህ ለሰሜን ኮሪያ የኒውክሌርም ሆነ የሚሳይሎች ትንኮሳዊ ሙከራ አሜሪካ እጅግ ፈጣን፣ ጠንካራና ቁርጥ ያለ እርምጃ ትወስዳለች ሲሉ ፒዮንግያንግን አስጠነቀቁ።

ሰሞኑን በዋይት ሃውስ ጉብኝት ላይ ላሉት የደቡብ ኮሪያው አዲሱ ፕሬዚዳንት ሙንጃኢ ኢን ጋራ በጋራ ከመከሩ በኋላ ለተሰበሰቡት ጋዜጠኞች አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ስታራምደው የነበረው ስልታዊ ትእግስት ተሟጣል ያሉ ሲሆን ለፒዮንግያንግ ከዋሽንግተን ሲሰጥ የነበረው ስልታዊ የትእግስት ዘመን አክትሟል በማለት ለደቡብ ኮሪያው አቻቸው ተናግረዋል።

ሆኖም ግን ከዚህ በዋሽንግተን እና በሴኡል መካከል ባላንጣቸውን ፒዮንግያንግን የሚመለከቱበት እይታ የተለያየ እንደነበረ ተገልጾ፣ በአሁኑ የደቡብ ኮሪያ አዲሱ ፕሬዚዳንት ሙንጃኢ ኢን እና በአሜሪካው ዶናልድ ትራምፕ መካከል ከፍተኛ የሆነ የሃሳብና የአመለካከት አንድነት እንደታየ በስፍራው የነበሩ ጋዜጠኞች የትራምፕን ማረጋገጫ ቃል በማጣቀስ ዘግበዋል።

ከሳምንታት በፊት ሰሜን ኮሪያ አህጉር ተሻጋሪ የኑክሌር አረር ተሸካሚ ሚሳኤል መሞከሯን አባይ ሚዲያ መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ የአሜሪካን መራሹና የሰሜን ኮሪያ ስድስት አስርተ ዓመታት በላይ የፈጀው ፍጥጫ የዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን መምጣት የሰሜን ኮሪያው ወጣት ቀደም ሲል ስልጣን ከአባቱ መውረስ ውጥረቱን ከእለት ወደ እለት እያከረረው እና እያባባሰው እንደሚገኝ ዲፕሎማቶች ይናገራሉ።