በወላይታና በሲዳማ ህዝቦች መካከል የመሬት ይገባኛል ጉዳይ ከሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማህበር የተሰጠ መግለጫ

0

ጁላይ 03 2017

በአሁኑ የኢትዮጵያ የመልክአምድር አቀማመጥ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የወላይታ ብሄረሰብ ይህንን ቦታና ስያሜ ይዞ የተቀመጠው ከብዙ ሺህ ዘመናት በፊት እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ያመለክታሉ። ይህ ጥንታዊ የሆነው ብሄረስብ በሁሉም አቅጣጫዎች መሰል ከሆኑ በርካታ ብሄረሰቦች ጋር የሚዋሰን ሲሆን፤ በሰሜን ከከምባታና ሃድያ፣ በሰሜን ምስራቅ ከኦሮሚያ፣ በምስራቅ ከሲዳማ፣ በደቡብ ከጋሞና ቁጫ እንዲሁም ደግሞ በምእራብ ከዳውሮ ጋር ይዋሰናል። ወላይታን ከነዚህ ሁሉ ብሄረሰቦች ጋር የሚያዋሰነው ወሰን የተወሰነዉ በታሪክና ብሄረሰቦቹ እርስ በርስ በመተማመን ያበጁት የጋራ ድንበር ነው እንጂ ማንኛውም የዉጭ አካል በመሀከላቸው ገብቶ ገመድ መትረው ችካል ቸክለው የወሰኑት አልነበረም። አሁን ወላይታ የሚገኝበት ወሰን፣ ድሮ በንጉሳዊ አገዛዝ በሚተዳደርበት ጊዜም ሆነ የወላይታ የንጉሳዊ ስርአት እና የራስ አስተዳደር እልህ አስጨራሽ በሆነው በምኒሊክ ጊዜ በተደርገው ጦርነት ተገርሰሶ ወላይታም የማዕከላዊ የኢትዮጵያ የመንግስት አካል ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ በማንኛውም መልክ ያልተሸራረፈ እና ያልተቀየረ ነበር። የወላይታም ብሔር እላይ ከጠቀስናቸው አጎራባችና ወንድም ከሆኑ ብሔረሰቦች ጋር እርስ በእርስ በመፈቃቀርና በመተሳሰብ የጋራ የሆኑ የታሪክ፣ የባህል፣ የማሕበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ እሴቶችን በመጠበቅ ፣ በማክበርና በመከባበር ለዘመናት አብረው ኖረዋል፤ አሁንም እየኖሩ ይገኛሉ። ይህ ሲባል ግን በማንኛውም ሁኔታ በወላይታና አጎራባች ከሆኑ ብሔረሰቦች ጋር ያለመግባባት ተፈጥሮ አያውቅም ማለት አይደለም። እንደማንኛውም በጋራ እንደሚኖር ማህበርሰብ እና የጋራ ድንበር ከሚኖራቸው ብሔረሰብ ጋር እንዲሁም በቤተሰብ ደረጃ ግጭት እንደሚፈጠር ሁሉ በወላይታና በእነዚህ በአጎራባች ብሔረሰቦች በተወሰነ መልኩ ከቀላል እሰከ መለስተኛ ግጭት በተለያዩ ጊዜያት ይፈጠር ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ግጭቶች ወይም አለመግባባቶች ብሔረሰቦቹ ለዘመናት ባካበቱት የጋራ ችግሮቻቸውን በጋራ የመፍታት ልምድ ካለማንም ጣልቃ ገብነት ይፈቱት ነበር። ይህ ባህላዊ ስርአትና ተቋም ህብረትሰቡ በመፈቃቅድ እና በመቻቻል እንዲኖሩ ከፍተኛ አስተዋጾ አበርክቷል። አሁንም ይህ የመፈቃቅድና የመቻቻል ባህል በተጠናከረ መልኩ ቀጥለው እነዚህን ብሔረሰቦች ይበልጥ እያቆራኛቸውና እያስተሳሰራቸው ይገኛል። ይህም በአካባቢያቸው ወቅታዊ የሆኑ ችግሮችን እንዲፈቱ በማገዝ የእለት ተእለት የኑሮ እንቅስቃሴያቸው ጤናማ በሆነ መልኩ እንዲቀጥል እጅግ እረድቶአል።

ሆኖም እዚህ ጋ አጽንኦት ሊሰጥው የሚገባው ጉዳይ ቢኖር ወላይታ ከሚያዋስናቸው አብዛኛውዎቹ ብሔረሰቦች ጋር በሚያገናኛቸው የድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች በሁሉም በኩል ተመሳሳይ የሆነ የአኗኗር ዘዴ ያላቸው ማለትም አብዛኛዎቹ በእርሻ ስራ የሚተዳደሩ ናቸው።  ይሁን እንጂ ወላይታን በምስራቅ በኩል የሚያዋስነው ወንድም የሆነው የሲዳማ ህዝብ በተለይ በድንበር አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ በአብዛኛው ከበዙ ዘመናት ጀምሮ በእንስሳት እርባታ የሚተዳደር አርብቶ አደር ነው። ይህ ወንድም የሆነው የሲዳም ህዝብ ለእንስሳቶቹ ሳርና ውሃ በሚያጥርበት በበጋ ወቅት የወላይታን ድንበር ተሻግሮ የወላይታ ቆላማና ለም መሬት ላይ እንስሳቶቹን በማሰማራት የወላይታን መሬት ይገለገል ነበር። የወላይታም ህዝብ እንግዳ በመቀበል ድንበር ተሻግሮ በግዛቱ እንስሳዎቹን እያሰማራ የሚገኘውን የሲዳማን ብሔረሰብ ካላንዳች ችግር የበጋ ወቅት እስኪያልፍ እንስሳቱን እንዲያሰማራ ይፈቅድ ነበር። የሲዳማ አርብቶ አደሮቹም የዝናብ ወቅት ሲመጣ ጓዛቸውን ጠቅልለው እንስሳቶቹን እየነዱ ወደመጡበት ወደ ሲዳማ ግዛት ተሻግረው ይመለሱ ነበር። ይህ ሁኔታ ለብዙ ጊዜ እየተደጋገመ በመምጣቱና እንግዳ ተቀባይ ከሆነው ከወላይታ ሕዝብ ጋራ እጅግ በመላመዳቸው አንዳንዶቹ ባህላችሁ ባህላችን፣ ወጋችሁ ወጋችን በማለት ጋብቻ በመመስረት ጎጆ ቀልሰው ኑሮአቸውን በወላይታ ግዛት ውስጥ እንዳደረጉ ይታወቃል። እንደዚህ ባለ ሁኔታ በወላይታ ግዛት ውስጥ መስፈር የጀመረው የሲዳማ ህዝብ ለረጅም ዓመታት በሚኖረበት ጊዜ አንዳችም የሆነ የግዛት ችግር ሳይኖርበት አስተናጋጅ የሆነው የወላይታ አስተዳደር በሚፈቅደው መሰረት አስፈላጊውን የነዋሪነት ግዴታውን እየፈጸመ ይኖራል።

ይሁን እንጂ፣ በቅርብ ጊዜ ከወደ ወላይታ አካባቢ የሚሰማው ወሬ እና እንዲሁም በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የሚዘገበው ዜና ከላይ ከጠቀስናቸው እውነታዎች የሚቃረኑ ሆነው ተገኝተዋል። በቅድሚያ እንስሳቶቹን ቀጥሎ ደግሞ ቀስ በቀስ ኑሮውን በወላይታ ታሪካዊ ግዛት ውስጥ መስፈር የጀመረውና አሁንም እየኖረ ያለው ወንድም የሆነው የሲዳማ ብሔረሰብ የሰፈረበት ቦታ ለሲዳማ ተላልፎ እንዲሰጥ መወሰኑ እየተነገረ ነው። ይህ ቦታ የወላይታ ብሄረሰብ ታሪካዊ ይዞታ ሲሆን በእንግድነት የሰፈረው የሲዳማ ብሔረሰብም አብሮ ተስማምቶ ተፈቃቅደው እና ተቻችለው ከመኖር ውጪ በማንኛውም መንገድ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ አንስቶ አያውቅም። ሁለቱም ወገኖች ድንበራቸውን እና ወሰናቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁና ከዚህ በፊትም በድንበር አካባቢም ሆን በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ የሚነሱ አለመግባባትን በጋራ የመፍታት የዳበረ ልምድ ያላቸው ናቸው።

በኣሁኑ ወቅት ያለዉ ሁኔታ የተፈጠረዉ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ በነዋሪዎች የጋራ መግባባት ሳይሆን በአስፈጻሚ አካላት ውሳኔ የወላይታ ታሪካዊ መሬት ለሲዳማ ተላልፎ እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑና ይህም የበላይ ኣካል ዉሳኔ በህዝቡ ላይ በግድ ወደመጫን እያመራ እንደሆን በስጋት ይነገራል። ይህ ኣካሄድ ሁለቱ ተስማምተውና ተፈቃቅደው የቆዩትን ብሔረሰቦች ወደ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል ስጋት አለ። ይህ ጉዳይ በጥንቃቄ ካልተያዘ በአካባቢው የማያባራ ግጭትን ሊፈጠር እንደሚችልና አላስፈላጊ የሆነ መናቆር ብሎም ደም መፋሰስ ሊያስከትል እንደሚችል አያጠራጥርም። ከዚህ የተነሳ አሁን እያጣጣሙት ያለውን ሰላምና ወግ እንዲፈርስ በማድረግ በአካባቢው ውጥረት ሊያነግስ ስለሚችል እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንኖር የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ይህንን በህዝቦች መካከል ግጭትን፣ ጥላቻንና አለመግባባትን ሊያስፋፋ የሚችል ኣካሄድን አስፈጻሚ አካላት ቆም ብሎ በማሰብ ሁኔታዉን በፍጥነት ብቻ ሳይሆን በፍትሃዊነትም ጭምር እልባት ማግኘት እንዲችል ይህን መሰል ሁኔታዎችን ፣በጋራ በመፍታት እጅግ የዳበረ ልምድ ያላቸውን የሁለቱን ብሔረሰብ አካላት እድል እንዲሰጣቸውና ከሁለቱም ብሔረሰቦች የተውጣጡ የሃገር ሽማግሌዎች፤ ምሁራንና ሌሎችም ታዋቂ ግለሰቦችን ያካተተ አካል ተመስርቶ ለጉዳዩ እልባት እንዲሰጡ ስንል በአጽንዎት እንጠይቃለን።

አስተማማኝ ሰላምና ፍትሃዊንት ለሁሉም ህዝቦች እንመኛለን!

በሰሜን አሜሪካ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ማህበር