በሲያትል ከተጠበቀው በላይ ነው ተመልካች የተገኘው – አቶ ጌታቸው ተስፋዬና ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ልዩ-ሪፓርታዥ ከሲያትል
3ኛ ቀኑን በያዘው የሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያውያን ስፖርት እና ባህል ፌስቲቫል ዝግጅትና ታዳሚ ከዚህ በፊት ከነበረው ዝግጅቶች ሁሉ በታዳሚው ብዛትና ድጋፍ ከፍተኛ እንደሆነ የኢሳፍና ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ተስፋዬ እና ከእሳቸው ጋር በስልክ ያገናኙኝ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ የተመካከሩ ይመስል በአንድ ድምጽ ተናገሩ።

image

ነገ በጎንደር፣ በጎጃም እና በሸዋ ህብረቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙትን ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳን ስለዝግጅቱ ኢንተርቪው እያደርኩ ሳለ በድንገት የኢስፋናን ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ተስፋዬን አይተው በጋበዙልኝ ፕ/ር ምክንያት ስለ ፌስቲቫሉ ዝግጅትና ጠቅላላ ሁኔታ አቶ ጌታቸው ከፕሮፌሰሩ ጋር ተመሳሳይ የሆነ መልስ በመስጠት አስደምመውኛል።

እንደ አቶ ጌታቸው ተስፋዬ አገላለጽ – የዘንድሮው የኢትዮጵያውያን ፌስቲቫል ከቀደምቶቹ ፌስቲቫሎች በተሳታፊዎች ቁጥር እጅግ በርክቶ እና በልጦ የተገኘ መሆኑን ገልጸው ስኬታማነቱንም ምናልባት የዋሽንግተን ዲሲው ተቀራራቢ ሳይሆን አይቀርም ሲሉ ገልጸዋል።

34ኛው የኢትዮጵያውያኖች እስፖርትና ባህል ፌስቲቫል ባለፈው እሁድ በደማቅ ሁኔታ ተጀምሮ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን እንደያዘ ይታወቃል። በዝግጅቱ ውስጥ ከተካተቱት ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ ሀምሌ 7ቀን ዓርብ የሚካሄደው የኢትዮጵያውያን የባህል ቀን [ኢትዮጵያን ካልቸራል ዴይ] እንደሆነ ገልጸው ለዚህ ልዩ ፕሮግራም ደግሞ እውቁን የታሪክ ጸሃፊ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳን በክብር እንግድነት ስለኢትዮጵያ ታሪክ ገለጻ እንዲያደርጉ መጋበዛቸውንም ገልጸውልኛል።

ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ ዓርብ ከሚካሄደው የኢትዮጵያውያን የባህል ቀን መድረክ ሌላ ነገ ሀሙስ በየጎንደር ህብረት፣ የጎጃም ህብረት እና የሸዋ ህብረት የጋራ ዝግጅት መድረክ ላይ ተገኝተው ስለ ኢትዮጵያዊ አንድነት፣ ታሪክ እና ከቋንቋ ይልቅ በክፍለ ሀገር ደረጃ የመደራጀትን አስፈላጊነት ለ3ቱ ድርጅቶች ገለጻ እንደሚያደርጉ ገልጸውልኛል።

ሆኖም የሁለቱም ምሁራን የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ እና የኢሳፋናው ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ተስፋዬ የተናጥል ግን አቻ ተመሳሳይ ቃል – የዘንድሮው የሲያትሉ ፌስቲቫል በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ ከተጠበቀው በላይ ታዳሚን በመሳብ ስኬታማ ሆኗል የሚል ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ከነገ ጀምሮ እጅግ ወሳኝ እና ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት የእግር ኳስ ውድድሮችን እናካሂዳለን ያሉኝ አቶ ጌታቸው ተስፋዬ ዛሬ ምሽት ደግሞ በጥበብ ዘርፍ ሀገሩን ለዓመታት በማገልገል ላይ ያለውን አርቲስት ሻምበል በላይነህን ለማክበር የክብር ምሽት አዘጋጅተንለታል ሲሉ ገልጸውልኛል።

እንደ አቶ ጌታቸው ተስፋዬ አገላለጽ አርቲስት ሻምበል በላይነህ ለሀገሩ በታማኝነት እና በጽናት በሙያው ያገለገለ መሆኑን አውስተው በተለይም ዘንድሮ፣ ይላሉ አቶ ጌታቸው፣ ሻምበል በላይነህ ከአዲስ ዘፈን ጋር የቀረበ እና ለኢሳፋናም የተለየ አንድ ዘፈን በማቅረብ ልዩ ሀገራዊ ድርሻውን የተወጣ አርቲስት ነው ሲሉ ይገልጻሉ።

ኢሳፋና በየዓመቱ ለሚያካሂደው ፌስቲቫል 3 የክብር እንግዶችን እንደሚጋብዝ ባህሉ እንዳደረገ የገለጹት አቶ ጌታቸው ከእግር ኳስ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የነበረው አቶ ፋንታ መኮንን ከሀገር ቤት ከአትሌቲክሱ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፣ ከዲያስፖራ እና በኪነ-ጥበብ አርቲስት ሻምበል በላይነህ እንደተመረጡ ገልጸው ከአርቲስቱ በስተቀር ሁለቱ በተለያየ ምክንያት መገኘት እንዳልቻሉ ገልጸውልኛል።

የዓለም አቀፍ ተቋም [የንግድ ድርጅት] በሆነው ሁበር እስፖንሰር መደረጋቸው ሌላው የዚህ ዓመት ፌስቲቫል ልዩ ውጤት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ይህን መሰሉ እስፖንሰርሺፕ ህዝባችንን ምንም መዋጮ እንዳንጠይቅ ይረዳናል ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከመቼውም ጊዜ በላይ ያየለበት ነው ያሉኝ ደግሞ የኦሮሞ እና አማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ መጽሃፍ ደራሲ የሆኑት ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ ናቸው።
ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያዊነትን እና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በስታዲየሙ ለተሰበሰበው ህዝብ በተዘጋጀላቸው የተለያየ መድረክ ለማስተማር እንደተጋበዙ ገልጸው በህዝቡ ዘንድ ያየሁት ሀገራዊ ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀይሎ የተገኘበት መሆኑን አይቼዋለሁ ሲሉ ገልጸውልኛል።

እንደ ፕ/ር ፍቅሬ አገላለጽ – ሰዎች በቋንቋ እና በአካባቢ ብቻ ተወስነው ከመደራጀት በክፍለ ሀገር ደረጃ ቢደራጁ ቀጥለው ያንን ክፍለ ሀገራዊ ድርጅትን ሀገራዊ ማድረግ ይቻላቸዋል ይላሉ።

ነገ ሀሙስ ሀምሌ 6ቀን ከጎጃም፣ ጎንደር እና ከሸዋ ከተውጣጡ ማህበሮች ጋር ገለጻ እንደሚያደጉ ገልጸው በማግስቱ ዓርብ ደግሞ የኢትዮጵያን ካልቸራል ዴይ ተብሎ በተሰየመው እለት ስለ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ አንድነታዊ ታሪክን እንደሚያቀርቡ ገልጸውልኛል።

ከፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጋር ያደርኩት ቆይታ አልተጠናቀቀም – የነገውን ውሎዋቸውን እና የዓርቡን ተክታትዬ እንደማቀርብ እየገለጽኩ ጽሁፌን እደመድማለሁ።