የቀን ገቢያችን 100 ብር ሆኖ በ600 ብር ገቢ ግብር ተጣለብን ሲሉ የአዲስ አበባ ነጋዴዎች የምንኖረው በሲኦል ነው አሉ

ምስል ከፋይል

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የአዲስ አበባ አነስተኛ ነጋዴዎች በተለምዶ አጠራር ደረጃ “ሐ” ተብለው የሚታወቁት አዲሱን የግብር ተመን መንግስት የእለት ገቢያችንን ሳያገናዝብ የጣለብን የማያሰራን ግብር ነው ሲሉ በክፍተኛ ምሬት ገለጹ።

በደረጃ “ሐ” የተመደቡ እነዚህ አነስተኛ በንግድ ስራ ላይ ከተሰማሩ ነጋዴዎች አንደበት የተሰማው እሮሮ የብዙዎችን ልብ የሰበረ ሀዘን እንደሆነ ከታሪካቸው ፍሰት መረዳት ይቻላል።

ለቪ.ኦ.ኤዋ ጽዮን ግርማ ስሙን ደብቆ ታሪኩን የተናገረው አንድ በላፍቶ ክፍለ ከተማ ያለ ነጋዴ ስላለበት ችግር ሲገልጽ “እኔ ጸጉር ቤት ነው ያለኝ – ሁለት ወንበር ያላት – ገማቾቹ በቀን 600 ብር ታስገባለህ አሉኝ – በእነሱ ስሌት ብንጓዝ ሁለታ ወንበር ያለምንም እረፍት ለ22 ሰዓታት ብትሰራ የተጠቀሰውን ገንዘብ ማግኘት ይቻላል” ካለ በኋላ ስለነባራዊው ገቢው ሲገልጽ “በቀን ከ5 ጊዜ በላይ መብራት ይጠፋል፣ በሳምንት እስከ 4 ቀን በመብራት ምክንያት ስራ የለም፣ በዚህ ላይ ያለነው የከተማዋ ዳር ሃና ማርያም ነው፣ እንዴት አድርገን ነው በቀን የ600 ብር ገቢ ልንቆጥር የምንችለው?” ሲል ምሬቱን ይገልጻል።

ከወራት በፊት የኢትዮጵያ ገቢና ጉምሩክ ባለስልጣን ከ300 ሺህ ለሚበልጡ የአዲስ አበባ ነጋዴዎች [አብዛኞቹ ባለአነስተኛ ገቢ] የእለት ገቢና ወጪያቸውን በ30 ቀናት ውስጥ የሚያጠና የሰው ሀይል አዘጋጅቻለሁ ብሎ እንደነበረ አይዘነጋም።

እነዚህ ከ300 ሺህ በላይ የሆኑት የነጋዴውን ገቢና ወጪ አጥኚ ግብረ ሃይሎች በሰላሳው ቀን ውስጥ አጥንተናል ብለው በደመደሙት የግምት ተመን መሰረት መንግስት በነጋዴው ህብረተሰብ ላይ አዲስ የግብር ተመን ሰሞኑን ማወጁ ይታወቃል። ይህ አዲሱ የግብር ተመንም ከነባራዊው የገቢና ወጪ ሂሳብ ጋር ያልተሰላና ያልተሰራ በመሆኑ አሁን የተጣለብን የግብር ተመን የሚያሰራን ሳይሆን እንዳንሰራ የሚያግደን ነው ሲሉ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች ምሬታቸውን በከፍተኛ ሲቃና እንባ እየገለጹ ያሉት።

“እኔን በቀን የአንድ ሺህ ብር ገቢ ታገባለህ ብለው ነው የመደቡብኝ” የሚለው ሌላው የንፋስ ስልኩ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነጋዴ የጸጉር ቤቱ አይደለም በቀን አንድ ሺህ ብር አንድ አራተኛውንም ማግባት አይቻልም ሲል በምሬት ይገልጻል።

ወጣቱ ነጋዴ በአብዛኞቹ ነጋዴዎች እንደ የስራቸው እንቅፋት አድርጎ የመብራት መቆራረጥን የጠቀሰ ሲሆን ያለበትን አስከፊ ሁኔታም ሲገልጽ “አምና በሀምሌ ወር ውስጥ ከ2001 እስከ 2008 የኖርኩበትን እና ብዙ ብር ያፈሰስኩበትን ቤቴን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ስንጥርም ይዘን ሳንወጣ በላያችልን ላይ አፈረሱብን። የባእድ መንግስት የሚባለው የሳኡዲ መንግስት እንኳን ዜጎቹ ላልሆኑት የ90 ቀን ጊዜ ገደብ ሲሰጥ እኛ ግን በሀገራችን በራሳችን መንግስት የ9 ሰዓት ገደብ እንኳን ሳይሰጡን ቤታችንን በላያችን ላይ አፈረሱብን” በማለት ምሬቱን ገልጾ ሲደመድም “እኛ የት ሄደን እንኑር? በአሁን ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ማለት ሲኦል ውስጥ እንደመኖር ማለት ነው” ሲል ብሶቱን ለቪ.ኦ.ኤ ገልጿል።

ያለአቅማቸው የግብር ተመን የተጣለባቸው የአዲስ አበባ ደረጃ “ሐ” ነጋዴዎች የደረሰባቸውን ወገብ ሰባሪ የግብር ተመን አቤቱታ ሊያሰሙ ቢወጡ ሀገሪቷ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ስላለች የምታካሄዱት ሰልፍ ህገወጥ ነው ተብለው እንደታገዱ በመግለጽ ሊሰማን የሚችል ባለስልጣንም የለም ሲሉ ይገልጻሉ።

አሁን ስራ ላይ እየዋለ ያለው የግብር ተመን በአነስተኛ የገቢ ደረጃ ተመድበው ያሉትን ከ300 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ህይወት እንዳናጋ ከስፍራው የሚደርሰን ዘገባ ይገልጻል።