ኢትዮጵያ 120 የሶማሌ እስረኞችን ለሞቃዲሾ አሳልፋ ለመስጠት ስትስማማ ኬኒያ ሁለት የፖሊስ ሃይሏ በአልሸባብ እንደተገደሉባት ተገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና
ወንድወሰን ተክሉ

በአዲስ አበባ የስራ ጉብኝት ላይ ያሉት የሱማሊያው ጠ/ሚ ከኢትዮጵያው አቻቸው አቶ ደሳለኝ ሀይለማርያም በኩል ኢትዮጵያ 120 ሶማሊያውያን እስረኞችን ለሞቃዲሾው መንግስት አሳልፋ ለመስጠት መስማማታቸውን ገለጹ።

የሱማሌው ጠ/ሚ/ር ሀሰን አሊ ሀሬ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ሲሆን ከመሪዎቹ ስብሰባ መጠናቀቅ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ቤተመንግስት በማቅናት ስምምነቱን እንደፈጸሙ ለማወቅ ተችሏል።

ሆኖም ጠ/ሚ/ር ሀሰን አሊ በእሳቸው መንግስት እና በኢትዮጵያው አቻቸው መካከል የተደረገው ስምምነት ምን ዓይነት እስረኞች እንደሆኑ በዝርዝር የገለጸው ነገር እንደሌለ ይታወቃል።

በሞቃዲሾ ያለው የሶማሊያ መንግስት የአዲስ አበባው መንግስት ታዛዥና ተባባሪ በመሆን ለቁጥር የሚያታክቱ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ስደተኞችን እያፈነ ለአዲስ አበባው መንግስት በመስጠት ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሱማሌ መንግስት የወደብ ከተማ በሆነችው ኪስማዩ በአልሸባብ ታጣቂዎች ላይ በከፈተው ማጥቃት 13 የአሸባሪውን አባላት መገደላቸውን የገለጸ ሲሆን የማቾቹንም አስከሬን በኪስማዩ ከተማ አደባባይ ላይ አውጥቶ ማሳየቱም ተገልጿል።

ከኪስማዩ 90 ማይል ርቀት ላይ ባለችው የኬኒያ የደሴት ከተማ ላሙ የአልሸባብ ታጣቂዎች በከፈቱት ማጥቃት ሁለት የኬኒያ ፖሊሶች መገደላቸውና 7ቱ ደግሞ የደረሱበት ያልታወቀ መሆኑን ኬንያ ስታስታውቅ፣ ሃላፊነቱንም አሸባሪው ሃይል አልሸባብ እንደሚወሰድ ገልጿል።