ዶ/ር መረራ ጉዲና ያቀረቡት መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

0

ታዋቂው ፖለቲከኛ የኦሮሞ ፌደራሊስት ሊ/መንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና የተከሰሱበት ክስ ከአርበኞች ግንቦት 7 ከፕ/ሮ ብርሃኑ ነጋ ከአቶ ጃዋር ከኢሳትና ከኦኤም ኤን ተነጥሎ እንዲታይላቸው ያቀረቡት መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ዛሬ አርብ በዋለው ችሎት ውድቅ አድርጎታል።

ፍርድ ቤቱ ምስክሮች የሚቀርቡት በሁሉም ተከሳሾች ላይ በመሆኑ ክሱ ተነጣጥሎ መቅረብ የለበትም ምስክሮች መጉላላት አይገባቸውም በሚል መቃወሚያውን ውድቅ አድርጎታል። ክሱ የግንቦት7 እና ኦነግ ልሳኖች በሆኑት የመገናኛ ብዙሃን ቅስቀሳ አድርገዋል፣ በተነሳው አመጽም ንብረት ወድሟል፣ ወንጀሉ በግብረአበርነት የተፈጸመ ስለሆነ የተመሰረተባቸው ህገመንግስታዊውን ስርዓት በሃይል መናድም በህግ የሚያስጠይቅ በመሆኑ ጉዳዩ በክርክር ሂደት ይታያል በማለት ፍርድ ቤቱ መቃወሚያውን ውድቅ ያደረገባቸውን ምክንያቶች ገልጿል።

በውሳኔው ያልተደሰቱት ዶ/ር መረራ “እንደምታውቁት እኔ የታሰርኩት በፖለቲካ ነው፤ የታሰርኩት መንግስት ይቅርታ በጠየቀበት የመልካም አስተዳደርና የካድሬዎች ችግር ነው፤ እኔ የታሰርኩት ለኦሮሞ ህዝብ ስለታገልኩ ነው፤ እኔ የታሰርኩት ለኢትዮጵያ ህዝብ ስለታገልኩ ነው፤ የታሰርኩት ለሃቀኛ ፌደራሊዝም እና ነጻ የፍትህ ስርዓት እንዲሰፍን ነው“ በማለት ተናግረዋል።

ዶ/ር መረራ እርሳቸው በጸረ ሽብር አዋጁ ስላልተከሰሱ የምስክሮች ስም ዝርዝር እንዲሰጣቸው ጠይቀው የነበሩ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ “የጸረ ሽብር አዋጁ ለምስክሮች ጥበቃ ይደረግ ይላል፣ በሌሎች ክሶችም ላይ ይህ ህግ መስራቱና አለመስራቱን በተመለከተ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትርጓሜ እንዲልክልንና እሱንም ለማየት ለሃምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ“ ሰጥቻለሁ በማለት ተነስቷል።

በሌላ በኩል ከአርበኞች ግንቦት7 ጋር በተያያዘ ከተከሰሱት መካከል፣ 39 ተከሳሾች “እኛ አሸባሪዎች አይደለንም፣ የነጻነት ታጋዮች ነን፣ አላማችንን አንክድም ቀጠሮም አንፈልግም ፍረዱልን ሳይሆን ፍረዱብን አታመላልሱን” ያሉ ሲሆን 42 ተከሳሾች ደግሞ የይቅርታ ደብዳቤ መጠየቃቸው ታውቋል። እስር ቤቱ ይቅርታ የጠየቁትን ይቅርታ ካልጠየቁት በመለየት ይቅርታ ባልጠየቁት ላይ ስቃይ እየፈጸመ ነው።

39ኙ እስረኞች በበኩላቸው ይቅርታ የጠየቁት አካሎች እኛ ያልተናገርነውን እንደተናገርን አድርገው ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ድርጅት በመናገራቸው ይቅርታ እንዲጠየቁና ጉዳዩ በሚዲያ እንዲነገርላቸው ጠይቀዋል።