የኬኒያ ተቃዋሚዎች በደህንነት ሚኒስትሩ ድንገተኛ ሞት ጥርጣሬያቸውን ገለጹ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የኬኒያ የሀገር ውስጥና የደህንነት ሚኒስትር ሜ/ጄ ጆሴፍ ካይሰሪ አማሟት ሁኔታ እንዳጠራጠራቸው በመግለጽ መንግስት በአስቸኳይ የአስከሬን ምርመራን አካሂዶ ለቤተሰባቸውና ለኬኒያውያን እንዲገልጽ ተቃዋሚዎች ጠየቁ።

ማቹ የደህንነት ሚኒስትር በጤናማነታቸው የሚታወቁ ሲሆን አርብ እለት በቦማስ ኬኒያ ሆቴል ተመግበው ካረን ባለው ቤታቸው እንደደረሱ ባደረባቸው ብርቱ ህመም ምክንያት ወደ ካረን ሆስፒታል የተወሰዱ ቢሆንም ህይወታቸው አርብ ለሊት ለቅዳሜ አጥቢያ ከለሊቱ 7፡00 ሰዓት እንዳለፈ ታውቋል።

የኬኒያው ፕሬዚዳንት በምኒስትሩ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ድንጋጤ ከገለጹ በኋላ ወደ ሟች ቤተሰብ ፈጥነው በመሄድ መንግስታቸው በሚ/ሩ አማሟት ዙሪያ ፈጣን ምርመራ ያካሂዳል ሲሉ ቃል ሰጥተው ነበር። የመንግስት ደህንነት ቢሮ የማቹን ሚ/ር አስከሬን ምርመራ እሁድ እንደሚካሄድ ለቤተሰባቸውና ለኬኒያውያን ገልጾ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ምርመራው ሰኞ [ዛሬ] እንዲካሄድ መወሰናቸው ተገልጿል።

ኬኒያ በመጪው ነሀሴ 8 ቀን 2017 ለምታካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ዘመቻ በተወጠረችበት በአሁኑ ሰዓት የደህንነት ሚ/ሩ ድንገተኛ እና ያልተጠበቀ አማሟት ኬኒያውያኑን በድጋጤ ውስጥ የጣለ መሆኑ ታይታል።

በምህጻረ ቃል ናሳ (National Supper Alliance NASA) አመራሮች በሚ/ሩ አማሟት ላይ ያደረባቸውን ጥርጣሬ በመግለጽ መንግስት ይህንን የሚያጣራ መልስ ማቅረብ አለበት ብለዋል።

የኬኒያ ደህንነት ፖሊስ (Criminal Investigation Department/CID) ቢሮ ትናንት እሁድ ከሚንስትሩ ጋር የመጨረሻ ሰዓታት ንኪኪነት ካደረጉ ሰዎች ውስጥ አስር ያህሉን ጠርቶ ቃል መቀበሉን ገልጿል። ሚ/ሩ የተመገቡበት የቦማስ ኬኒያ ሆቴል አስተናጋጆች፣ ምግብ አብሳዮች፣ ቦዲጋርዳቸውና ሾፌራቸው ቃላቸውን እንዲሰጡ ከተደረጉት ውስጥ የተጠቀሱ ናቸው።

ኬኒያውያኑ ሚ/ሩ በምግብ መመረዝ ተገድለዋል የሚል እድምታን ሲያንሸራሽሩ የታዩ ሲሆን የህልፈታቸው ምክንያት ግን ሰኞ በሚካሄደው አስከሬን ምርመራ ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል።