በአማራው ክልል ትጥቅ የማስፈታቱ እርምጃ በድጋሚ እንዲከሽፍ መደረጉ ተገለጸ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በአማራው ክልል በጎንደር፣ በጎጃም እና በሸዋ በኮማንድ ፖስቱ የታቀደው ድንገተኛ ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ መክሸፉ ተነገረ

የአማራው ክልል ካድሬዎች፣ ሚሊሺያና ፖሊሶች እንዲሳተፉበት በተደረገው በዚህ የኮማንድ ፖስቱ ድንገተኛ ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ በክልሉ ካድሬዎችና ሚሊሺያዎች ድጋፍ እንዳጣም ተገልጿል።

ኮማንድ ፖስቱ በሶስቱ የአማራ ክልሎች አንቃሽ፣ እብነት፣ ጃዊ፣ ሸበል፣ ደራ እና ሰሜን ሸዋ ወረዳዎች ገበሬውን “የመሳሪያ ምዝገባ እና የመሳሪያ ግብር”ብሎ ለመሰብሰብ ቢሞክርም እንዳልተሳካለት ከስፍራው የደረሰን ዜና ይገልጻል።

በዚህ የመንግስት ጥሪ አልስማማ ያለውን የክልሉን ገበሬ በድንገተኛ ሰበራ ቤት ለቤት እየሄደ ትጥቅ ለመግፈፍ የዘመተው የኮማንድ ፖስቱ ሰራዊት በገበሬው ንቁ ተከላካይነት እና እምቢተኝነት ዘመቻው መክሸፉን ለማወቅ ተችሏል። በተለይም በሰሜን ጎንደር አውራጃዎች እና በጎጃም ያሉት የስርዓቱ ካድሬዎች፣ ሚሊሺያና ፖሊስ ሃይል ከኮማንድ ፖስቱ የተሰጣቸውን ገበሬውን አባብሎና አታሎ ትጥቅ የመግፈፍ ግዳጅ “ገበሬውን አትነካኩት፣ ብሶት ያለበት ነው” በማለት ታዛዥ መሆን እንዳልቻሉ ተግልጿል።

ኮማንድ ፖስቱ በጎንደር አንቃሽ ፣እብናትና በጎጃም ጃዊ ባሰማራው ሰራዊቱ በግዳጅ የትጥቅ ገፈፋ ለመፈጸም ሰራዊቱን ቢያሰማራም ሊሳካለት እንዳልቻለ የተነገረ ሲሆን በሌሎች የጎጃምና ሸዋ ወረዳዎች ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ በሌሊት ቤት ለቤት እየዞረ ሊፈጽም ያቀደው የመሳሪያ ገፈፋ እንዳልተሳካለት የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል። የአማራው ክልል በተለይም በሰሜን ጎንደር አውራጃዎች ነፍጥ አንስተው እየታገሉ ያሉ አርበኞች ያሉበት ክልል ሲሆን ህዝቡ በደረሰበት መንግስታዊ በደልና ጭቆና ተማሮ ለመብቱ የተነሳበት እንደሆነ ይታወቃል።

ይህንን ህዝባዊ ዓመጽና ህዝባዊ ጥያቄን በስልጣን ላይ ያለው ገዢው ፓርቲ በወታደራዊ ሀይል ጨፍልቄ እቆጣጠራለሁ በማለት ክልሉን በአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ስር በሰራዊት ማጥለቅለቁ የሚታወቅ ነው።