በታሪክ ከባዱ በተባለለት ድርቅ በምስራቅ አፍሪካ 27 ሚሊዮን ሕዝብ ለርሃብ ተጋልጧል ተባለ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በምስራቅ አፍሪካ በታሪክ ከባዱ በተባለ ድርቅ ምክንያት ከ27 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የምግብ እርዳት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን የተ.መ.ድ ሰብዓዊ መብት ድርጅት አስታወቀ።

እንደ ድርጅቱ ገለጻ ከሆነ ላለፉት ስድስት ወራት ብቻ አራት ሚሊዮን ሕዝቦች በድርቅ ምክንያት የተሰደዱ ሲሆን በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ደግሞ ሌሎች ሶስት ሚሊዮን ሕዝቦች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ይገልጻል።

ከምስራቃዊው የአፍሪካ ቀጠና የተጎጂው ቁጥር ይበልጥ በአፍሪካ ቀንድ እንደሚያይል ያስረዳው የተ.መ.ድ ሪፖርት በኢትዮጵያ ብቻ ከ7.7 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በድርቁ ምክያት ለረሃብ ተጋልጧል ሲል ይገልጿል።

ሆኖም ይህ የተራበ ህዝብ ቁጥር በያዝነው ሀምሌ ወር እና ነሀሴ ወር ውስጥ ወደ አስር ሚሊዮን ይደርሳል ሲል ገልጿል። ሶማሊያና ኤርትራ በቀጣናው ለርሃብ የተጋለጠ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር በመያዝ ከኢትዮጵያ ቀጥለው ይገኛሉ።

የአፍሪካ ቀንድን ያካተተው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ለረጅም ጊዜ ታይቶ ባልታወቀ ከፍተኛ ድርቅ እንደተጠቃ ሪፖርቱ ገልጾ ነዋሪው በዚህ አደጋ ምክንያት ከትውልድ ስፍራው ለመፈናቀልና ለመሰደድ ተገዷል ብሏል።

በዚሁ በተያያዘ ዜና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በአፍሪካ ቀንድ ለተከሰተው ድርቅ ወለድ ርሃብ 600 ሚሊዮን ዶላር በእርዳታ መልክ መንግስታቸው መመደቡን ዋይት ሃውስ ያስታወቀ ሲሆን ዓለም ዓቀፉ የምግብ ድርጅት በበኩሉ ከለጋሽ ሀገራት የተሰጠውና ቃል የተገባው እርዳታ ከተረጂው ቁጥር ጋር ስለማይመጣጠን ለጋሾች አሁንም እርዳታቸውን እንዲለግሱ ሲል ጥሪውን አሰምቷል።