ቁርጥ ግብር፤ የህውሓት ገጀራ (በካሳ አንበሳው)

የሰሞኑ የማህበራዊ ሚዲያ አጀንዳ አዲስ አበባ ውስጥ በአነስተኛ የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች ላይ የተጣለው ከፍተኛ “ግብር” ነው፤ ይህ ግብር “ቁርጥ ግብር” ወይንም “Presumptive tax” በመባል ይታወቃል፤ “ቁርጥ ግብር” ታማኝ ያልሆኑ ዜጋ የሚቀላበት (የሚወገድበት) ሎሌ የሚተከልበት የህውሓት አንዱ  ስውር ገጀራ ነው:: ይህ ገጀራ ከወያኔ የዕዝ ሰንሰለት ውጭ በንግድ ተሰማርተው የተገኙትን ዜጎች ይቀስፋል፤ የወያኔ ዕዝ <<የህብረት ስራ ማህበራት፣ ጥቃቅን እና አነስተኛ  ኢንተርፕራይዝስ ወ.ዘ.ተ>> በሚባሉ ስያሜዎች የሚታወቁት ናቸው፤ የወያኔ ገጀራው ከሰገባው የሚመዘዘው በአመት አንዴ ነው፤ ብዙ ዜጎችን ሙት እና ቁስለኛ ሳያደርግ ወደ ሰገባው አይመለስም፤ የዚህ ገጀራ ሰለባ ከሆኑት መካከል ጋሽ መሐመድ ሐሰን አንዱ ናቸው::

ጋሽ መሐመድ የአካባቢውን ነዋሪ ልብስ በማጥበብ፣ በማሳጠር እና በመጠገን ስምንት ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ታታሪ ዜጋ ናቸው፤ ከልጅነት እስከ እውቀት የማውቃቸው በዚህ ሙያቸው ነው፤ አንድ ክፉ ቀን የህውሓት እጅ የጋሽ መሐመድን ሱቅ በርቅሳ ግድግዳው ላይ <<ማኔን፣ ቴቄል፣ ፋሬስ> ብላ ጻፈች፤ <<መዘንኩህ (በታማኝነት ሚዛን) ቀለህም ተገኝህ፣ ሱቅህም ለታማኝ ሎሌ ተሰጠች>> ስትል ነው፤  ጋሽ ማሜ ሰምተውት እንጂ አየተውት የማያውቁትን ገንዘብ እንዲከፍሉ ተጠየቁ፤ 5 ሺህ ብር! ጋሽ መሐመድን ብዙም አልደነገጡም፤ ባለመረበሻቸው የተገረሙ ወዳጅ እና ዘመዶች ጠጋ ብለው ሲጠይቋቸው ለሁሉም የሚሰጡት መልስ ተመሳሳይ ነው፤ <<5 መቶ ቢሉኝ ከልጆቼ ጉሮሮ ነጥቄ፣ ተበድሬ ወይም እቁብ ገብቼ  ለመክፍል በደከምኩ፤ አላህ ይስጣቸውና 5 ሺህ ብር ብለው ከዚህ ሁሉ ድካም ገላገሉኝ>> ይላሉ:: ጋሽ ማሜ መሰዋት ሆኑ!

ሌላው የህውሓት ቆንጨራ <<የሙያ ብቃት ማረጋገጫ>> በሚባል ይታወቃል፤ እንጀረ በመጋገር የምትተዳደር አቅመ ደካማ እናት ሳትቀር በህውሓት ሰራዊት <<የሙያ ብቃት ማረጋገጫ>> ስለሌለሽ አክንባሎሽን ስቀይ መባሏ የቅርብ ቀን ትዝታ ነው፤ እንግሊዘኛ ተናገር የተባለ ጊዜ ምላሱ ከትናጋው የሚጣበቅበት ካድሬን (ጸጋዬ በርሄን መጥቀስ ይቻላል) ባለ ሙሉ ስልጣን አንባሳደር አድርጋ የምትሾም ህውሓት አንድን እናት የእንጀራ ጋገራ  የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ካላመጣሽ ምጣድሽን እሰብራለው ማለቷ ግርምታን ያጭራል::

ለቱርክ፣ ለሳውዲ፣ ለህንድ እና ለሎች የውጭ ሃገር <<ባለሃብቶች>> ከሊዝ ነጻ መሬት፣ 70% ብድር እና የአምስት አመት የትርፍ ግብር እፎይታ አዘጋጅታ “ኑ” << ሙሉሄ በኩሉሄ>> የምትለው ወያኔ ምነው ዜጎች ላይ እንዲህ ጨከነች? ጎዳና ላይ አንጥፎ አልያም መስኮት ቀዶ ጉሮሮውን ለመድፈን የሚወተረው ዜጋ ላይ ምነው ልቧ ደነደነ? ብሎ መጠየቅ ተበጊ ነው፤ አጭሩ መልስ <<የኢኮኖሚ ነጻነቱ የተደፈጠጠበት ህዝብ ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ እንደሆነ ስለምትረዳ፤ የኢኮኖሚ ነጻነቱ ዲሞክራሲያዊ መብትን እንደሚያስከትል ጠንቅቃ ስለምታውቅ>> የሚል ይሆናል:: በዚሁ ወደ ፍሬ ጉዳያችን (የኢትዮጵያዊያንን የኢኮኖሚ ነጻነት ያለበትን ደረጃ ወደ መዳሰሱ) እንዝለቅ::

የኢኮኖሚ ነጻነት (Economic Freedom) ዜጎች በፖለቲካ አመለካከት፣ በዘር (በጎሳ ወይም ብሄር)፣ በሃይማኖት ወ.ዘ.ተ አድሎ ሳይደረግባቸው በነጻነት፣ በመረጡትና በፈለጉት የኢኮኖሚ መስክ እንዲሰማሩ (እንዲሳተፉ) የሚያስችል የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ማዕቀፍ ነው::

የዜጎች የኢኮኖሚ ነጻነት በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 41 “የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህላዊ መብቶች” ውስጥ የተካተት ቢሆንም በሃገራችን ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት እጦት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ:: ይህንን ከሚጠቁሙት መረጃዎች መካከል ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን (Heritage Foundation) እና የዎል ስትሪት ጆርናል (The Wall Street Journal) በተባሉ ተቋማት ከ1995 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ በየአመቱ የሚወጣው የኢኮኖሚ ነጻነት ደረጃ (Economic Freedom index) ሪፖርት ዋነኛው ነው:: ይህ አህዛዊ መለኪያ የሚያመለከተው ዜጎች በሃገራቸው ውስጥ በነጻነት (በምርጫቸው)፣ ያዋጣኛል ባሉት የኢኮኖሚ መስክ ሃብታቸውን እና እውቃታቸውን ተጠቅመው (ሌሎች ዜጎችም ይህንኑ የማድረግ መብታቸውን ሳይጋፉ) የማምርት፣ የመሽጥ እና የመለወጥ መብትን ነው::ከስር ከተመለከተው ከግራፉ ማየት እንደሚቻለው በ2013 እና 2014 (እ.ኤ.አ.) ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጭቆና ካለባቸው ሃገራት ውስጥ ተካታለች::

በቅርቡ ይፋ የሆነው የ2017 (እ.ኤ.አ). ይህ የሃገራት የኢኮኖሚ ነጻነት ደረጃ ሪፖርት ኢትዮጵያን ከዓለም 142ኛ፤ ከሰሃራ በታች ካሉ 46 የአፍሪካ ሃገራት ደግሞ 31ኛ አስቀምጧታል:: በዚህ ሪፖርት ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት ከሌለባቸው ሃገራት ውስጥ ተካታለት:: ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ሙስና ሲሆን ሌላው ደግሞ መድሎ እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል:: ሪፖርቱ የመንግስት ባለስልጣናት በከፍተኛ ሙስና ውስጥ የተዘፍቁ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ብድር፣ የመስሪያ ቦታና የስራ ቅጥር የሚያገኙት የገዥው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች መሆናቸውን አስቀምጧል::  “በመንደር ለማሰባሰብ” (Villagization) እና <<ለልማት>> በሚሉ ሰንካላ ምክንያቶች በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ያለፍላጎታቸው ከቀያቸው እንዲነሱ መደረጉ ኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ነጻነት ከሌላባቸው ሃገረት ተርታ ያሳለፍት ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ይሄው ሪፖርት ያትታል:: ሪፖርቱ በመንግስት የተጣለው የግብር አይነትና መጠን የዜጎችን የመስራት፣ የመቆጠብና ኢንቨስት የማድረግ አቅምንና ፍላጎትን በከፍተኛ ደረጃ የሚፍትን መሆኑን በመጥቀስ ይህም ሃገሪቷን የምጣኔ ሃብት ነጻነት ከሌላቸው ሃገራት ግርጌ እንድትሰለፍ ማድረጉን ያብራራል::  ይህ ሪፖርት የግብር ስርዓቱ የዜጎችን የኢኮኖሚ ነጻነት ይጻረራል ሲል የሚጠቅሰው የስራ ቅጥር ግብር ጣሪያ 35% እና የንግድ ስራ ትርፍ ግብር 30% መሆኑን ጠቅሶ ነው:: ይህንን ሪፖርት ያወጡት ተቋማት ሰፋ ያለ ጥናት አድርገው ቢሆን ኑሮ ውጤቱ ከዚህ እጅጉን የከፋ ይሆን እንደነበር አያጠራጥርም:: ለምሳሌ ያክል በቁርጥ ግብር ስርዓት (Presumptive taxation system) በአነስተኝ የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች ቆጥረውት አይደለም አይተውት የማያውቁትን የገንዘብ መጠን በግብር መልክ እንዲከፍሉ እንደሚጠየቁ፤ በዚሁም ምክንያት ንግዳቸውን ለመዝጋት እንደሚገደዱ፤ መንገድ ዳር ጫማ በመጥረግ የሚተዳደሩ ዜጎች ጭምር በወር 12 ብር እንደሚከፍሉ (እንደሚቀሙ)በሌላ በኩል ደግሞ እነ ሃጎስ ከቀረጥ ነጻ ወደ ሃገር ቤት ያስገቧቸውን የኮንስትራክሽን ማሽኖች ለመንግስት ፕሮጀክቶች ሳይቀር በሰዓት እስከ 1,000 ብር በነጭ ወረቀት እያከራዩ በግብር መልክ የሚከፍሉት ሰባራ ሳንቲም እንደሌለ ግንዛቤ ውስጥ አልገባም:: ይህቺ ናት ኢትዮጵያ!

ratio
ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን እና የዎል ስትሪት ጆርናል በጣምራ ከሚሰሩት ጥናት በተጨማሪ ለጀርመን የልማት ተቋም በዶ/ር ቲልማን አልቴንበርግ (Tilman Altenburg) ተጠንቶ “Industrial Policy in Ethiopia” በሚል ርዕስ 2010 እ.ኤ.አ. የታተመው ጽሁፍ መደምደሚያ ላይ ከደረሰባቸው ነጥቦች አንዱ የሚከተለው ነው::

“Business and politics are still strongly entwined in Ethiopia…………… party-affiliated endowments have taken many of the business opportunities left for private engagement. It is not always clear to what extent political considerations reflect the business strategies of those firms, and vice versa.” (pp. 29).

“በኢትዮጵያ ንግድ ስራና ፖለቲካ እርስ በርስ ተወታትበዋል……………….. የግል ኢንቨስተሮች ሊሰማሩባቸው የሚገቡ (የሚችሉ) አብዛኞቹ የስራ ዘርፎች በፖለቲካ ፓርቲዎች የንግድ ድርጅቶች ተይዘዋል፤ የነዚህ በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚተዳደሩት የንግድ ድርጅቶ ስትራቴጂ ነው የፖለቲካ ውሳኔን የሚቀድመው (የሚወስኑት)? ወይንስ የመንግስት ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው የንግድ ድርጅቶችን ስትራቴጂ የሚወስነው? የሚለው ብዙ ጊዜ ግልጽ ሁኖ አይታይም:: ” (ገጽ 29)
ይሄው ጥናት እንደሚያመለክተው ሼክ መሃመድ አላሙዲንን ጨምሮ የተወሰኑ ባለሃብቶች ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በንግድ ሽርክና እና ሎሎች እንዲህ ነው ተበለው ሊጠቀሱ በማይችሉ (ለህዝብ ግልጽ ባልሆኑ) ጥቅማጥቅሞች መተሳሰራቸውን ጠቅሶ እነዚህ አካለት ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል የበለጠ የኢኮኖሚ ነጻነት እንዳላቸው ይገልጻል::

“Business, Politics, and State in Africa: Challenging the Orthodoxies on Growth and Transformation” በተሰኝው መድብል ውስጥ ተካቶ “Ethiopia: Rent-seekers and Productive Capitals” በሚል ርዕስ የወጣው የቲም ኬልሴል (Tim Kelsall) ጥናት ከላይ የተጠቀሰውን የቲልማን አልቴንበርግን መደምደሚ ያጠናክረዋል:: የቲም ጥናት የህውሓት ንብረት የሆነውን የEFFORT አመሰራረትና ሂደት በስፋትና በጥልቀት ከተነተነ በኋላ EFFORTትን በተለየ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች አይወሰኑም ማለት አይቻልም ሲል ይደመድማል:: ለቲም ከልሴል ጥናት ማረጋገጫ የሚሆነው የዛሬ ሶስት የአመት ገደማ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ነው:: በዚህ ቃለ መጠይቅ በዛን ወቅት የEFFORT ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ወ/ሮ አዜብ መስፍን “መለስ ከመሰዋቱ በፊት የአምስት ዓመት የትግራይ ኢንደስትሪ በEFFORT እንዴት መፈጸም እንዳለበት የጻፍው ስትራቴጂ ነበር” ማለታቸው ፖለቲካዊ ውሳኔዋት ለEFFOR እና EFFORትን ለመሳሰሉ ተቋማት ያደሉ ናቸው ወደሚለው መደምደሚያ ይወስዳል::

በሌላ በኩል አክሴል ቦርችግሪቪንክ (Axel Borchgrevink) የተሰኙ ምሑር “Emerging Economies and Challenges to Sustainability: Theories, Strategies, Local Realities” በተሰኘው መድብል “Ethiopia: Rapid and Green Growth for All?” በሚል ርዕስ በ2014 እ.ኤ.አ. ባሳተሙት የጥናት ጽሑፍ ገዥው ፓርቲ የሚከተለውን የኢኮኖሚ ሞዴል ዜጎችን በእኩል ደረጃ ተሳታፊ ማድረግ እንደተሳነው አሳይተው ይህም በዜጎች መካከል ያለውን የገቢና የሃብት ልዩነት እንዳሰፋው አትተዋል::
ከላይ ከተጠቀሱት ጥናቶች መረዳት እንደሚቻለው የገዥው ፓርቲ፣ የመንግስት ባለስልጣናትና ደጋፊዎች በተሰማሩበት የንግድ ዘርፍ በነጻ ገበያ ስርዓት ተወዳዳሪ ሆኖ መዝለቅ አዳጋች ነው:: በገዥው ፓርቲ ስር ለተሰበሰቡት ነጋዴዎች የሚደረግላቸውን የተለየ መድሎን ተቋቁሞ ገበያ ውስጥ መዝለቅ የቻለ ነጋዴ የፖለቲካ ስልጣንን ተገን ባደረገ አሻጥር (የግድያ ዛቻንና እስርን ይጨምራል) ከገበያ እንዲወጣ ይደረጋል:: ይህ አይነት ፖለቲካዊ ደባ ከተፈጸመባቸው ባለሃብቶች መካከል የኢተዮጵያ አማልጋ ሜትድ ሊሚትድ ባለቤት የነበሩትን አቶ ገብረየስ ቤኛን መጥቀስ ይቻላል:: አቶ ገብረየስ ተሰማርተውበት የነበረው ዋነኛው የንግድ መስክ በአሁኑ ወቅት በገዥው ፓርቲ ድርጅቶች (ጉና፣አምባሰል፣ ወንዶ እና ዲንሾ) በሞኖፖል የተያዘው የማዳበሪያ ንግድ ነው:: አቶ ገብረየስ ቤኛ በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ESAT) ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለ መጠይቅ በፖለቲካ አሻጥር ለ1 ቢሊዮን 700 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ተዳርገው በመጨረሻም የሃሰት ውንጀላ እና ዛቻ በመበርታቱ ንግዳቸውን ዘግተው በስደት ይኖሩባት ወደነበረችው አሜሪካ መመለሳቸውን አስረድተዋል::

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የኢኮኖሚ ነጻነት የግለሰብን ብሎም የማህበረሰብንና የህዝብን ገቢና የኑሮ ደረጃን በየውቅቱ እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጾ ያደርጋል:: የኢኮኖሚ ነጻነት በተከበረበት ሃገር ዜጎች ለስራ ቅጥር የሚታጩት በትምህርት ደረጃቸው፣ በስራ ልምዳቸውና በችሎታቸው ነው:: ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ነጻነት በታጣበት ሃገር ዜጎች ለስደት ይዳረጋሉ:: የዜጎቻችንን ህይወት እየቀጠፍ ላለው ስደት ዋነኝው ምክንያት የኢኮኖሚ ነጻነት እጦት መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው:: የስርዓቱ ባለስልጣናት “ለዜጎች ሰደት መንስሄው የግንዛቤ እጦት ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርቶ መቀየር ይቻላል” ሲሉ ድንበር በማቋረጥ ላይ ያሉ ዜጎች በበኩላቸው “ሃገራችን ውስጥ ሰርተን መቀየር ይቅርና በነጻነት ሰርተን መብላት አልቻልንም” በማለት ያማርራሉ:: የጀርመን ራዲዮ የአማረኛው ፕሮግራም ክፍል “መፍትሄ የሚያሻው የስደት አባዜ” በሚል ርዕስ ጥቅምት 28, 2008 ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ከሳውዲ ተመላሽ ኢትዮጵያዊ ይህንኑ ነው ያረጋገጡት::

የኢኮኖሚ ነጻነት ባልተረጋገጠባት ሃገር ህዝቦች በእኩልነት ተሳታፊና ተጠቃሚ የሆኑበት ልማት ሊመጣ አይችልም:: የዜጎች የኢኮኖሚ ነጻነት ባልተከበረበት ሃገር ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች (ነጻነቶች) ይከበራሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው:: እንደዘርፉ ምሁራን ገለጻ ኢኮኖሚውን የተቆጣጠረ እና የህዝቦችን የኢኮኖሚ ነጻነት የደፈጠጠ መንግስት የህዝብን ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ጭምር እንደተቆጣጠረ ይገልጻሉ:: ዜጎች በፖለቲካ ፓርቲ አባልነታቸውና ደጋፊነታቸው ሥራ የሚቀጠሩ፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው ከሥራ የሚሰናበቱበት ሃገር ሰባዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ይከበራል ተብሎ አያታሰብም:: ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን ከገዥው ፓርቲ የንግድ ድርጅቶች (ከጉና፣አምባሰል፣ ወንዶ እና ከዲንሾ) ብቻ እንዲገዛ የተገደደ ገበሬ የልቡን ይናገራል ተብሎ አይጠበቅም:: የኢኮኖሚ ነጻነት የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዳይሽራረፉ የሚረዳ ትልቁና ዋነኛው መደላድል ስለሆነ ፖለቲካኞችም ሆኑ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች እና ተቋማት ለዜጎች የኢኮኖሚ ነጻነት ቅድሚያ ሰጥተው መንቀሳቀስ ይገባል።