የትግራይ ምሁራን የኤርትራ ችግር ይፈታ ወይም ትግራይ ካሳ ይከፈላት ጥያቄ ሲፈተሽ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ልዩ-ዘገባ

**መንደርደሪያው ዜና-

የትግራይን ሕዝብ በመወከል ሁለት የክልሉ ምሁራን የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር ያለውን ችግር በቶሎ መፍታት ካልቻለ ለትግራይ ክልል የጦር ጉዳተኝነት ካሳ ሊከፍል ይገባል ሲሉ ለጠ/ሚ/ር አቶ ደሳለኝ ሃይለማርያም ደብዳቤ መላካቸውን ቪ.ኦ.ኤ ዘግባል።

እንደ ሁለቱ የትግራይ ምሁራን አገላለጽ ከሆነ ላለፉት 17ዓመታት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለው ጦርነትም ሆነ ሰላም አልባ ፖሊሲ[No war,No peace]ትግራይና አፋር ክልል በጣም የተጎዱ ናቸው የሚል ሲሆን በተለይም የጉዳቱ ጫና በትግራይ ላይ እጅግ ያየለ በመሆኑ መንግስት ካሳ ሊሰጠን ይገባል ባይ ናቸው።

የቪ.ኦ.ኤዋ ጋዜጠኛ አዳነች ፍስሃዪ ከሁለቱ ምሁራን ጋር ቆይታ አድርጋ ለአየር ካበቃችው አፍሪካን ነክ ፕሮግራም ላይ የሚከተለውን ዘገባ አቅርቢያለሁ

**1ኛ-በጦርነቱ ተጎጂ በመሆን ትግራይ የአንበሳውን ድርሻ የወሰደች ስለመሆኑ
ከ17 ዓመት በላይ በፈጀው በኢትዮጵያና ኤርትራ ወይ ሰላም ወይም ጦርነት የሌለው ግንኙነት ትልቁን የጉዳት ጫና ትግራይ ተሸከምላች ይላሉ ሁለቱ የትግራይ ምሁራን አቶ መሀሪ ዮሃንስ በመቀሌ ዮንቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና የእስትራቴጂክ ጥናት መምህር እና አቶ አስፋው ገዳሙ በአዲስ አበባ የኢትዮ-ቴልኮም ሰራተኛ የሆኑት ምሁራኖች።
ሆኖም ምሁራኑ ይህንን ትግራይ በሁለቱ ሀገሮች ባልተፈታ ችግር ምክንያት ዋጋ እየከፈለችበት ነው ላሉት ተጋሪ ጎረቤት የአፋርን ክልል እንደ ተጎጂ አድርገው ቢያቀርቡም በካሳ ጥያቄያቸው ላይ ግን እንዳላካተታትም ከንግግራቸው መረዳት ተችላል።

በትግራይ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ደካማ ነው፣ኢንቨንስትመንት የለም፣መንግስት አንዳችም ነገር ለትግራይ አልሰራም፣በመሀል ሀገር በተነሳ ብጥብጥ ትግራይ ከላይና ከታች [በሻእቢያ እና በመሀል ኢትዮጵያ የተነሰው አመጽ]የተወጠረ ጠላት ሆናል የሚሉት እነዚህ ምሁራን መንግስት በአፋጣኝ መፍትሄ ሊፈልግለት ይገባል ባይ ናቸው። እንደ መፍትሄ ብለው ያቀረቡትም ሁለቱም ምሁራን በመጀመሪያ ደረጃ ለሰላማዊ መፍትሄ ቅድሚያ እንደሚሰጡ ገልጸው ካልተቻለም በሚያስፈልገው የሀል እርምጃ የአስመራውን መንግስት መለወጥ ይገባል ባይ ናቸው።

በአሰብ ወደብ የግብጽ የጦር ካምፕ ለማቃቃም ስፍራ ማግኘት፣የሳኡዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሰላሳ ዓመት ኮንትራንት አስብን ተከራይተው የጦር ካምፕ መመስረታቸው ምሁራኖቹ እጅግ፣እጅግ ለኢትዮጵያ በተለይም ደግሞ ይላሉ ለትግራይ ህዝብ ህልውና አደገኛ በመሆኑ መንግስት በዝምታ ሊያየው አይገባም ባይ ናቸው።

የሁለቱ ምሁራን የትግራይ በመንግስት መካስ አለባት በሚለው እምነታቸው ለጠ/ሚ/ር ቢሮ ጥያቄያቸውን አስገብተው መልስ እየተጠባበቁ እንደሆነም ተናግረዋል።

ይህ የሁለቱ የትግራይ ምሁራን ጥያቄና እይታ ዋና እድምታው ምን ይመስላል? ምንንስ ያሳያል ?ዓላማውስ ምንድነው?የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተን እንድንያ ያደረገናል።
**2ኛ-ትግራይ ካሳ ይገባትል?

ከ70ሺህ በላይ ንጹሃን ያለቁበት የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት መንስኤ መንግስት ወረራ በፈጸመው የሻእቢያ ጠብ አጫሪነት ምክንያት ነው ቢልም እውነታው ግን የሻእቢያ የወረራ ጥቃት የተፈጸመው መንግስት በራሱ ሲያራምደው በነበረው ያልተገባ እና ወረራውን ባበረታታ ሚዛናዊ ባልሆነው ግንኙት ምክንያት እንደሆነ ግልጽ ነው። ከጦርነቱ በፊት በመንግስት እና በሻእቢያ መካከል የነበረው በአንድ እንትን የመፍሳት ግንኙነትና ምስጢራዊ ስምምነት መፍረስ ወረራውን እንደግፈጠረ ይታወቃል።
በጦርነቱ ትግራይ የውጊያ ቀጠና እንደመሆና መጠን ከሌሎች ክልሎችና አካባቢዎች ይበልጥ የተጎዳች መሆና ሀቅ ነው። ጉዳቱ ግን የሰው ሀይል ጉዳት ሳይሆን ጸጥታና ነጻነትን የተመለከተ ይሆንና በውጊያው ግን ታላቁን መስዋእትነት በመክፈል ሌሎች ክልሎች ከትግራይ በእጅጉ የበለጠ መስዋእትነት የከፈሉ በመሆናቸው የምሁራኑን ትግራይ ይበልጥ ተጎድታለችን ሀሳብ ውድቅ ያደረገዋል።

በአንጻሩም ጦርነቱ በትግራይ ላይ ጉዳት ብቻ ሳይሆን ታላቅ ጠቀሜታን አጎናጽፎ እናያለን። ከጦርነቱ ወዲህ-ትግራይ ከዘጠኙም የፌዴራል ክልሎች በኢኮኖሚ፣በኢንቨስትመንት፣ልዩ-መንግስታዊ ድጎማ በማግኘት፣ህብረተሰቡ በመታጠቅ፣ከ200ሺህ በላይ መከላከያ ሰራዊት መስተናገጃ በመሆን፣የመከላከያ፣ፖሊስ፣ደህንነት፣የሚሊሺያና የካድሬዎች ልዩ ማደራጂያና ማጠናከሪያ ተግባሮችን እና …ወዘተ በማግኘት ከጉዳታ ይልቅ የተጠቀመችው በልጦ እናያለን።

ሌላው ሊታለፍ እማይገባው ዋናው ነጥብና ቁም ነገር-የፌዴራሉ መንግስት በራሱ ቁጥጥርና መሪ ተዋናይነት በሚገዛውና በሚቆጣጠረው ህዝብና ግዛት ውስጥ ላደረሰው ጥፋትና በደል የመካስ ተግባራዊ ልምድ ባልዳበረበትና ባልታወቀበት ሀገር የትግራይ ምሁራን የትግራይ መካስ አለባት አቤቱታ ከጉንጭ አልፋነት የማይዘል ሆኖ እናገኘዋለን።[ለመሆኑ አይደለም በኤርትራ ጦርነት-ሱማሊያ ተወስደው ላለቁት ከ20ሺህ በላይ ወገኖቻችን ቤተሰቦች ካሳ ተከሰጥታል?]

3ኛ-የምሁራኑ ዓላማና በጥያቄያቸው ውስጥ ያለው እውነትስ ምንድነው?

የምሁራኑ ጥያቄ በእርግጥ መሰረት አልባ አይደለም። ያስጨነቃቸውና ያሳሰባቸው ጉዳይም የካሳው ጉዳይ ሳይሆን የትግራይን የወደፊት[የቅርብ ፊታችን]ጉዳይ እንደሆነ እንረዳለን። የግብጽ እና የሌሎች ዓረብ ሀገራት ቀይ ባህርን መቆጣጠር፣የጦር ሃይላቸውንም በአሰብና በምጽዋ ማቃቃም መቻል ትልቁ ራስምታታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህንን ጭንቀትና ስጋት አባብሶ መንግስትን “ከኤርትራ ጋር ያለህን ችግርመፍታት በምትችለው በአስቸካይ ፍታ አሊያም ትግራይን ካሳ ክፈል” ብለው እንዲጠይቁ ያደረጋቸው የመሀል ሀገር አመጽ ብለው የገለጹት ክስተት ነው።

ከደቡባዊታ የኢትዮጵያ ክፍል ያስገመገመው የአመጽ ድምጽ የምሁራኑ ስጋትና ጭንቀት ምንጭ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። እንደመፍትሄም አምነውበት ለተፈጻሚነቱ እየጠሩለት ያለው የደቡቡን ውጥረት ማረገቢያ መንግስት መውሰድ ያለበትን የማሻሻያ ፖሊሲዎችን እንዲያደርግ ከመጠይቅ ይልቅ የሰሜኑን የተዘጋ የድንበር በር የሚያስከፍት ጦርነት ወይም የተፈለገው እንዲደረግ መጠየቅ ሆናል።

የምሁራኑ ሰሜናዊውን ተዋሳኛቸውን ግዛት ከስጋት የነጻ መሆን አለበት ባይ ናቸው። ከሶስት ወራት በፊት አቶ ደሳለኝ ሀይለማርያም መቀሌ ተገኝተው “የትግራይ ህዝብ ችግር እሚፈታው ከኤርትራ ጋር ያለን ችግር ሲፈታ ነው” ብለው ነበር። ብዙም ሳይቆዩ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ላይ ሲያራምደው የቆየውን ፖሊሲ መለወጥ በማስፈለጉ አዲስ ፖሊሲ እያጠናን እና እያዘጋጀን ነን ሲሉ ተደመጡ።

ሁለቱ የትግራይ ምሁራንም ለጥያቄያቸው መንግስት በኤርትራ ላይ ያለውን ፖሊሲ የሚተካ አዲስ ፖሊሲ በቅርቡ ይፋ ያደርጋል ብሎ እንደመለሰላቸው ተናግረዋል። ይህኑኑ አዲሱን ኤርትራን የተመለከተ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ መንግስት ከወዲሁ አስፈጻሚ ኩነቶችን እያዘጋጀ ነው ብለን ልንናገር እንችላለን።

ከደቡባዊው ትግራይ ባሉት የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ የተነሳውን ህዝባዊ አመጽ እንደ የትግራይ ህዝብ ህልውና አደጋ እና ስጋት አድርገው ምሁራኑ ቢያስቀምጡትም ለሰሜኑ የኤርትራ ስጋት መፍትሄ ብለው ያስቀመጡለት ጉዳይ አይተን ለደቡቡ ምንም አለማለታቸውን ስንሰማ የምሁራኑን ምሉእ መፍትሄ ፈላጊነት ጎዶሎ ያደርገዋል።

በእርግጥ የምሁራኑ መፍትሄ ጎዶሎነት ብቻ ሳይሆን የመንግስት እና የእንወክለዋለን ያሉት የትግራይ ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ተቃጣብን ላሉት የህልውና ስጋት የተለሙለት መፍትሄ እንደሌለም ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

**መደምደሚያ-

አቶ መሀሪ ዮሀንስ እና አቶ አስፋው ገዳሙ-የትግራይን በዚህ መንግስት ስር ምንም ተጠቃሚ ያልመሆንን አባባል በተጨባጭ ለማሳየት ብዙ ሲጥሩ ተስተውለዋል።በንግግራቸው ሁሉ የትግራይ ህዝብ በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ በላቡ እና በወዙ ለፍቶና ጥሮ ያገኘውን እየዘረፈ የሚበላ እየተባለ ነው የሚል ምሬት አስምተዋል። በሀገር ውስጥ የተከሰተውን ህዝባዊ ጥያቄና አመጽ ከትግራይ ህዝብ ህልውና አንጻር ስጋት እንደሆነ ከመግለጽ የዘለለ-በፍትሃዊ ጥያቄነቱ እና ብሎም የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ስለወሰዱት እርምጃ ኢ-ፍትሃዊነት የተነፈሱት ነገር የለም።

የተፈጠረውን ችግር እውቅና በመስጠት ይስማሙና ለመፍትሄው ደግሞ የችሩ ምንጭ ከሆነው መንግስት ዘንድ ለውጥ ይከሰት -እርምት ይካሄድ የሚል ሳይሆን መፍትሄውን ኤርትራን ነጻ የስጋት ቀጠና በማድረግ እንደሆነ የሚያምኑ ሆነዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረባቸው የህልውና አደጋ ስጋት መፍትሄውም እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሆን ሲገባው እንዴት ሆኖ ከውጭ ጎረቤት ሀገር ዘንድ እንዳለ በማመን ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንደፈለጉ ግራ ቢያጋባም ጤናማና ትክክለኛ እንዳልሆነ እናውቃለን።