በመላ አገሪቱ ያሉ ነጋዴዎች የእለታዊ ገቢ ግብርን እየተቃወሙ ነው

0

በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳር፣ በወልድያ፣ በሻሸመኔና በደቡብ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ዜጎች በግምት ላይ የሚጣለውን ግብር በመቃወም ላይ ሲሆኑ በምስራቅ ሃረርጌ በጨለንቆና በጭሮ ከተማ ደግሞ ህዝብ ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞውን አሰምቷል። ነጋዴዎቹ ከገቢያቸው ጋር ያልተመጣጠነ ግብር እንዲከፍሉ መደረጋቸውን የግብር መከፈያ ጽ/ቤትን በመክበብ ሲቃወሙ ውለዋል።

ስቱዲዮ በገባንበት ሰአት ወኪላችን ባደረሰን ዘገባ ደግሞ በቦሌ ክ/ከተማ አንዲት ግብር ከፋይ በድንጋጤ ህይወቷ አልፏል። የከተማው አጠቃላይ ካድሬዎችም ግብር ከፉዩን የማረጋጋት ስራ ብቻ ቅዲሚያ ሰጥተው እንዲሰሩ ታዘዋል።

ባለፉት ሳምንታት በመርካቶ ራጉኤል ቤተክርስቲያን ዙሪያ ያሉ 250 አካባቢ ነጋዴዎች ሱቅ ለመዝጋት አቅደው የነበረ ቢሆንም፣ ካመፃችሁ በቤተክርስቲያኗ ግፊት የኪራይ ውል እናቋርጣለን የሚል ማስፈራሪያ ከካድሬዎች በመሰጠቱ እቅዱ ሳይሳካ ቀርቷል። የገዢው ፓርቲ ሚዲያዎችም ባለተለመደ ሁኔታ የግብር ስሌቱን በማስረዳት ፕሮግራም ላይ ተጠምደዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ ነጋዴዎች አቤቱታ በሚያሰሙበት ወቅት የኢህአዴግ ካድሬዎች እንደ አቤቱታ ሰሚ አካል ሆነው በመቅረብ፣ “እናንተ ግብሩን አሁን ገብሩና ጭማሪውን ህዝቡ ላይ ጫኑት፣ ዞሮ ዞሮ እናንተ አትከፍሉትም” በማለት፣ ነጋዴዎች በህዝቡ ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲያደርጉ በመምከር ላይ መሆናቸው ታውቋል።