የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች ናቸው ተብለው በሽብርተኝነት ክስ በወያኔ ፍርድ ቤት የቀረቡ 39 ወጣቶች በንቅናቄው ራዕይና ተልዕኮ እንደሚያምኑ በድፍረት መግለጻቸው ታወቀ

0

ከአምስት  ቀን በፊት መውጣት የነበረባቸው በቴክኒካል ችግር ዘግይተው የወጡ ዜናዎች    

ህወሃት  ሰኔ 30 ቀን 2009 አ.ም አዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሽብርተኝነት ወንጀል ክስ መሥርቶባቸው ያቀረባቸው 39 ወጣቶች የአርበኞች ግንቦት 7ን ራዕይና ተልዕኮ ከልባቸው አምነውበት ድርጅቱን የተቀላቀሉ መሆናቸውንና ንቅናቄው እያካሄደው ያለው የነጻነት ትግል ፍትሃዊ እንደሆነ አሁንም ድረስ የሚያምኑበት መሆናቸውን ክሳቸውን ለማየት በተሰየሙ ዳኞች ፊት በድፍረት መግለጻቸው አቃቤ ህጉንና ዳኞቹን እንዳሸማቀቀ ከፍርድ ቤቱ አካባቢ ለትንሳኤ ሬዲዮ የተላከው  መረጃ አመለከተ።

በዛሬው የወያኔ ፍርድ ቤት ውሎ  ይህንን አቋማቸውን በድፍረት የገለጹት እነዚህ ወጣቶች ህወሃት የህዝባችንን የትግል ሞራልና በአገዛዙ ላይ የማመጽ ፍላጎትን ለመግደል አርበኞች ግንቦት 7 ን ከድተው  በሠላምዊ መንገድ እጃቸውን ለመንግሥት ሠጥተዋል በማለት በቅርቡ ሰፊ ቅስቀሳና ፖሮፖጋንዳ ሲነዛባቸው ከነበሩ 80 ወጣቶች መካከል ያሉ ናቸው። የፍርድ ውሎውን በመከታተል መረጃውን ለዝግጅት ክፍላችን ያስተላለፈው ምንጫችን እንደሚለው ሠላሳ ዘጠኙም ወጣቶች አንድ ላይ ሆነው ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ እኛ ሽብርተኞች አይደለንም፤ አርበኞች ግንቦት 7ን የተቀላቀልነው ወደንና አምነንበትነው፤ አሁንም ወደፊትም አርበኞች ግንቦት 7 ነን በማለት ሲገልጹ በዳኞችና አቃቤ ህጉ ፊት ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ ይታይ እንደነበርም ታዉቋል።

የኢትዮጵያ ቴለቪዥንና በቅርቡ በነ ዶክተር ደብረጽዮን ተከፍቶ የሥርጭት ሥራውን የጀመረው የኢኤን ኤን ቴለቪዥን ወጣቶቹ ተወናብደው አርበኞች ግንቦት 7ን መቀላቀላቸውን ሲናገሩ እንደነበርና አሁን ተጸጽተው እጃቸውን ሲሰጡ አገሪቱ ውስጥ ባዩት ልማትና ዕድገት እጅግ መደነቃቸውን ያለ ሃፍረት በማከታተል ሲዘግቡ ሰንብተዋል።

የተከሳሾቹን ቃል ለመስማት ዛሬ አርብ ፍርድ ቤቱ በተሰየመበት ሰዓት የመንግሥት ጋዜጠኞች እና የህወሃት ፕሮፖጋንዳ ሠራተኞች ህዝቡን ሊያደናግሩበት የሚችሉበትን የተከሳሾች የይቅርታ ጥያቄ ለመዘገብ አሰፍስፈው ሲጠባበቁ እንደነበር የዘገበው ምንጫችን 39ኙም አንድ ላይ ሆነው የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች ነን እንጂ ሽብርተኞች አይደለንም፤  ፍርድ ቤቱ ሊሰጠው የፈለገውን የጥፋተኝነት ፍርድ ምንም ሳያዘገይ ዛሬውኑ ያስተላልፍ ሲሉ በማየታቸው  በድንጋጤ ፍርድ ቤቱን ለቀው ወደ መጡበት መመለሳቸውን ማረጋገጡን ገልጿል።