ህወሃት በሃረር ከተማ ማክበር የጀመረው የዲያስፖራ ቀን ከፍተኛ ህዝባዊ ቁጣ እየቀሰቀሰ ነው

0

ህወሃት እስከፊታችን ሃምሌ 28 ቀን ለአንድ ወር ሃረር ከተማ ላይ ማክበር የጀመረው የዲያስፖራ ቀን ከማህበረሰባችን ወግና ባህል ውጪ የሆኑ አንዳንድ አጸያፊ ተግባራት ከጅምሩ ሲፈጸምበት በመታየቱ በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ቁጣ መቀስቀሱ  ከሥፍራው ካገኘነው መረጃ ለማረጋገጥ ተችሎአል።

የህወሃት ንግድ ድርጅቶችና የቅርብ ሰዎች በብዛት ተጠቃሚ ሊሆኑ በሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቶ ሃረር ላይ ሰሞኑን የተጀመረው የዲያስፖራ ቀን ለማክበር የተገኘው ሰው ብዛት ከወትሮው በጣም ያነሰ እንደሆነም ታውቆአል። በሥፍራው የሚገኙ ምንጮች በዘንድሮው በዓል ላይ ለመታደም እስከዛሬ የተገኙ የዲያስፖራ አባላት ቁጥር ከመቶ እንደማይበልጥ በዚህም የተነሳ ኑሮ የተመቻቸው የህወሃት አባላትና ደጋፊዎች ዲያስፖራውን መስለው በበዐሉ ላይ ለመታደም ከተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ወደ ቦታው እንደተላኩ ይናገራሉ።

ከዲያስፖራ የመጡ ናቸው የተባሉ አንዳንድ ሰዎች ከአገራችን ባህልና ወግ ውጪ ለህዝብ እይታ ግልጽ በሆኑ ሥፍራዎች እንዳንድ አጸያፊ ተግባራትን ሲፈጽሙ በመታየታቸው የከተማው ህዝብ ልጆቻችንን ምን አይነት አጸያፊ ባህል ልታስተምሩ ነው ይህንን በሽታችሁን ይዛችሁብን የመጣችሁት የሚል ጥያቄ በማንሳቱና ቁጣ በማሰማቱ ህዝብ ለማረጋጋት ሲባል ለአንድ ወር ታስቦ የተከፈተውን በዓል በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የአካባቢው ባለሥልጣናት ማስተባበያ እየሰጡ እንደሆነም ታውቆአል።

የዲያስፖራ ቀን እያለ ህወሃት በየአመቱ ማክበር የጀመረው በዐል ታሳቢ ያደረገው ኑሮአቸውን በውጪ አገር ያደረጉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በአገዛዙ ላይ እየፈጠሩት ያለውን ከፍተኛ ጫና ለማርገብ ሰዎችን በግል ጥቅም ለማማለል ታስቦ እንደሆነ ሲዘገብ ኖሮአል። ህወሃት የዲያስፖራ ቀን በማዘጋጀት በትናንሽ ጥቅማጥቅሞች የውጪውን ነዋሪ እቆጣጠራለሁ ብሎ ባወጣው ዕቅድ እስከ ዛሬ ማጥመድ የቻለው ቀድሞውኑ የአገርና የወገን ውርደት የማይሰማቸው፤  አብዛኛውን ጊዜያቸውን ወደ አገር ቤት በመመላለስ የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ የቆዩትን ብቻ እንደሆነ በሰፊው ይታወቃል።