ህወሃት እያራገበው ያለው የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ አገዛዙ ለገጠመው የገንዘብና የውጪ ሚንዛሪ ችግር እንደ መውጫ ቀዳዳ እየታየ መሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው

0

በግብርና መሪ ኢኮኖሚ ሰፊውን የአገራችን አርሶ አደር ተጠቃሚ ያደረገ ልማትና ዕድገት አስፍናለሁ በማለት ለአመታት ሲንቀሳቀስ የኖረው የህወሃት አገዛዝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገጠመውን ከፍተኛ የውጪ ሚንዛሪ ዕጥረትና የጥሬ ገንዘብ ችግር ለማቃለል ሲል ወደ ኢንዱስትሪ ተኮር ኢኮኖሚ ፊቱን ማዞር መጀመሩን እያሳወቀ መሆኑን  ለማወቅ ተችሎአል።

ህወሃት/ኢህአደግ እስከዛሬ በሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀደም ሲል የመሣሪያ ትግል ያካሂድ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የድጋፍ “መሠረቴ ነበር” በማለት በቃላት የሚሸነግለውን “ሰፊውን አርሶ አደር ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የግብርና መሪ ኢኮኖሚ እከተላለሁ” ሲል የቆየ ከመሆኑም በላይ በሃሰት በተፈበረኩ መረጃዎች ሚሊዮኔር የሆኑ አርሶ አደሮች ተፈጥሯል በማለት ለአገዛዙ ቅርበት ያላቸውን አንዳንድ ሰዎች የመሸልም ድራማ ሲያካሂድ ቆይቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገር ውስጥና የውጪ ባለሃብቶችን ትኩረት ለመሳብ ተብሎ በተለያዩ ከተሞች እየተገነቡ ባሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዜና፤ አገዛዙ ለበርካታ አመታት ሲያራግበው የኖረው  የግብርና መሪ ኢኮኖሚ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ከባለሥልጣናቱ አፈና በሥራቸው ከሚተዳደሩ ሚዲያዎች መሰማት እየተቻለ አይደለም።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችና አለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች አገራችን ውስጥ ህዝባዊ ተቃውሞ በስፋት መካሄድ ከጀመረበት ያለፈው ሁለት አመት ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሪ ዕጥረት አገሪቱን እንደገጠመው በመናገር ላይ ናቸው። መቀሌ ላይ የተገነባውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመመረቅ ወደ ሥፍራው ተጉዞ እግረ መንገዱን ከመቀሌ ነዋሪዎች ጋር ውይይት እንዳደረገ የተዘገበለት ሃይለማሪያም ደሳለኝ አገራችንን ገጥሟታል የተባለው የውጪ ምንዛሪ እጥረት የአገዛዙን አፍንጫ ሰንጎ እንደያዘ መስክሯል።

ባለፉት ወራት በሃይለማሪያም ደሳለኝ ተመርቀዋል የተባሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በሙሉ የተካሄዱት በቻይናና በህወሃት ጄነራሎች በሚመራው ሜቴክ ኩባንያ ብቻ እንደሆኑ ለማረጋገጥ ተችሏል። ሜቴክ የሚመራው በሳሞራ የኑስ የበላይነት ሲሆን ዋና ዳይሬክተሩ ሌላው የህወሃት የጦር  ብርጋዴር ጄነራል ክንፈ ዳኘው እንደሆነ ይታወቃል።