ያለዉ የእርዳታ ሃብት ክምችት ኢትዮጵያዉያን ሕጻናትን ለመርዳት የማያስችል መሆኑን እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ገለጹ

አባይ ሚዲያ ዜና
ናትናኤል ኃይለማርያም

በተፈጥሮ አደጋና በድርቅ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በሚደርሱት አደጋዎች ዙሪያ ለ12 አመት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረዉ በምህፃረ ቃል (MSF) ተብሎ የሚጠራዉ ቡድን የምግብ እጥረት ስለገጠመዉ ለአደጋዉ የተጋለጡትን ሕጻናቶች መርዳት የማይችልበት ሁኔታ ላይ መድረሱን ይፋ አድርጓል።

MSF ወይም ድንበር የለሽ ዶክተር ተብሎ የሚጠራዉ ግብረ ሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያና በሶማሊያ አካባቢ 68 ሕጻናት በተመጣጠነ የምግብ ዕጥረት ምክንያት የሞቱ መሆናቸዉን ሲገልጽ በዚህ ዘመን በቦታዉ ላይ የሚታየዉ የተመጣጠነ የምግብ ዕጥረት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ አይነት የተከሰተ መሆኑን ገልጿል።

MSF እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ ባለዉ ጊዜ ዉስጥ ሕፃናትን ለመርዳት እየሠራ ቢገኝም በተፈጠረዉ የምግብ ዕጥረት ሳቢያ ግን ሥራዉን አስቸጋሪ እንዳደረገበት ገልጿል።

በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በኬንያ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ ያለዉ የዝናብ መቀነስ የምግብ እጥረት ሊያስከትል እንደሚችል አንድ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ FEWS NET የተባለ ተቋም መግለጹም ታዉቋል።

ድርቁ በዘላኑ ማሕበረሰብ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ሲጠቁም በድርቁ ምክንያት ሰብሎች እንደሚደርቁ ክብቶችም የሚመገቡት ሊያገኙ እንደማይችሉ እና እንደሚሞቱም ጭምር አያይዞ አስረድቷል። የንጹህ ዉሃ አለመኖሩንም ተከትሎ ዉሃ ወለድ በሽታዎች መፈጠራቸዉ እና ኮሌራና ኩፍኝም በሕብረተሰቡ ዉስጥ መስፋፋታቸዉን እና በሺዎች የሚቆጠሩት በዚሁ በሽታ እንደተበከሉ አስረድቷል።

የተባበሩት መንግስታት የምግብ ፕሮግራም መሥሪያ ቤት ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት ሙከራ ያደረገ ቢሆንም የተረጂዉ ቁጥር መጨመር እና የሚገኘዉ እርዳታ በቂ ባለመሆኑ ምክንያት ሥራቸዉን በአግባቡ ሊወጡ አለመቻላቸዉን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ 7.8 ሚሊዮን ሕዝብ እርዳታ የሚጠብቅ በመሆኑ ከዚህ በተጨማሪም በዚህ በያዝነዉ ዓመት ብቻ ይኼ ቁጥር በ2 ሚሊዮን ጨምሯል።

በዚህ በያዝነዉ ወር ዉስጥ ያለዉ የምግብ ክምችት ሊያልቅ እንደሚችልና አሁን አዲስ እርዳታ ቢገኝ እንኳን በአሁኑ ሰዓት ምግብ ማግኘት ለሚገባቸዉ ሊደርስላቸዉ እንደማይችል WFP ገልጿል።