የኢትዮጵያ ቀን በቫንኩቨር ዛሬ በድምቀት ይከበራል

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በቫንኩቨር እና በአከባቢዋ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዛሬ በዌስበርን ፓርክ የኢትዮጵያ ቀንን በቤተሰባዊ እስፖርትና ባህል ፌስቲቫል እንደሚያከብሩ አቶ ከበደ አባተ ለአባይ ሚዲያ ገለጹ።

ለስምንተኛ ጊዜ በተዘገጃው በዛሬው የኢትዮጵያ ቀን ፌስቲቫል በዌስበርን ፓርክ በድምቀት እንደሚያከብሩ አቶ ከበደ ለአባይ ሚዲያ ገልጸው በዝግጅቱም የተለያዩ አዝናኝ ፕሮግራሞች ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ከሲያትል በመጡ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች እና በጋናውያን ሙሉ ባንድ የሙዚቃ ድግስ እንዳላቸው ተናግረው የተለያዩ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች፣ አልባሳትና እቃዎችም ለሽያጭ የሚቀርቡበት ዝግጅት እንዳለም አብራርተዋል።

የህጻናት መዝናኛ የሚሆን በዓየር የተሞላ ሸራ ላይ መንሸራተቻ ያዘጋጁ መሆናቸውን የገለጸችልን ደግሞ ከአስራ ስድስቱ አዘጋጅ ኮሚቴው አንዳ የሆነችው ወ/ሮ ናኒ ተስፋዬ ስትሆን ልጆቻችንን በኢትዮጵያ ባንዲራ ህብረ ቀለማት በሚያስውብ ንቅሳት ልናስውባቸው ተዘጋጅተናል ብላለች።

በፌስቲቫሉ ላይ የገመድ ጉተታ፣ የእንቁላል ውድድር የመሳሰሉ ቤተሰባዊ መዝናኛ መዘጋጀታቸውን ማወቅ የተቻለ ሲሆን ከ7 ሺህ እስከ 10 ሺህ የሚገመቱ በቫንኩቨር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ የተዘጋጀው ስምንተኛው ፌስቲቫል ገቢ የኮሚኒቲውን ማእከል ለመገንባት እንደሚውል ከአዘጋጆቹ መረዳት ተችሏል።

በአቶ ብስራት ሰብሳቢነት 16 አዘጋጅ ኮሚቴ የተዋቀረው ቡድን ላለፉት ሶስት ወራት ይህንን የዛሬውን የኢትዮጵያ ቀን ፌስቲቫል ለማሳካት ሲሰራ እንደቆየ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን ከኮሚቴው አባላት ውስጥም አቶ ኦሪዮን መንግስቴ፣ አቶ ደበበ ጋሉ፣ አቶ ሉሉ ከበደ፣ አቶ ከበደ አባተ፣ አቶ ሀሰን፣ አቶ ሄኖክ ወዘተ..እና ከ16ቱም ውስጥ ብቸኛዋ እንስት ኮሚቴ ወ/ሮ ናኒ ተስፋዬ እንዳሉበት ለማወቅ ተችሏል።