‎የአውሮፓ ኢትዮጵያውያን እስፖርትና ባሕል ፌስቲቫል ከአቻው የሲያትሉ ፌስቲቫል ምን መማር አለበት? [ከወንድወሰን ተክሉ]

0

እንደመንደርደሪያ-

34ኛው በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን እስፖርትና ባህል ፌስቲቫል በሲያትል በደመቀ ሁኔታ ባለፈው ሳምንት መከናውኑን አይተናል፣ ሰምተናልም። የአውሮፓው አቻ የኢትዮጵያውያኑ እስፓርትና ባህል ፌስቲቫልም ለ15ኛ ግዜ በኢጣሊያ ዋና ከተማ ሮም ለማካሄድ መዘጋጀቱን ከወጣው ፕሮግራም መርሃግብር ላይ ማወቅ የተቻለ ቢሆንም በፌስቲቫሉ ላይ ኢትዮጵያዊነትን ደምቆና አብቦ እንዳይታዩ የሚያደርጉ ክስተቶች በመስተዋላቸው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በዝግጅቱ ላይ እንዳይታደሙ የሚገልጽ ዜና ከዚያው ከአውሮፓ መሰማት ተችላል።

ይህ ክስተት እንዴት ሊፈጠር ቻለ? አማራጭ መፍትሄውስ ምንድነው? በአውሮፓ ያሉ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ የራሳቸውን ባህል በዓመታዊው የእስፓርትና ባህል ፌስቲቫል በነጻነት አዘጋጅተው ለማክበር ምን ማድረግ አለባቸው በሚሉት ነጥቦች ዙሪያ የዛሬን ጽሁፌን እንዲያጠነጥን አድርጌያለሁ።

**አንደኛ-ለምንድነው የሮሙ ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያውያን እንዳይሳተፉ እየተገለጸ ያለው?
የዚህን ዓመት በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን እስፖርትና ባህል ፌስቲቫል ስልጣን ላይ ባለው የኢህአዴግ መንግስት ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ እጅ አዘጋጅነት የተዘጋጀ መሆኑን ተክትሎ ሀገር ወዳዱ ኢትዮጵያውያን በፌስቲቫሉ ላይ ለመገኘት እንዳልቻሉ መረዳት ተችሏል። ድርጊቱ [የመንግስት እጅ በማህበሩ ውስጥ መታየት] በእርግጥም በማስረጃ የተደገፈ እና እውነት የሆነ ቢሆንም ግን መሆን የማይገባው እንደሆነ በቅድሚያ ልንስማማበት የሚገባ ነጥብ እንደሆነ ይሰማኛል።

የመንግስት ጣልቃ ገብነት የትም ቢሆን ሊከሰትና አፍጥጦ መጥቶም ሊጋፈጥ ይችላል። በሰሜን አሜሪካው የኢትዮጵያውያን እስፖርትና ባህል ፌስቲቫል [ESFNA] ላይ በተመሳሳይ መልኩ ከ2011 ጀምሮ በሼህ ሁሴን መሀመድ አል-አሙዲን እና በኢህአዴግ ጣልቃ ገብነት ለ5 ዓመት የዘለቀ ተግደርዳሮትን በመፈጸም ማህበሩን ለመንጠቅ ከፍተኛ ሙከራ እንደተካሄደ ሁላችንም እናውቃለን።

ሆኖም የሰሜን አሜሪካው የESFNA ማህበር ቦርድ አመራሮችና ከሁሉም በላይ ሰፊው የዲያስፖራው ማህበረሰባችን ባደረጉት ያላወላወለ ሀገራዊ ቁርጠኝነት አቋም ተለጣፊው የመንግስት ማህበር ተንኮታኩቶና ከስሞ ዘንድሮ ስርዓተ ቀብሩ መፈጸሙ ታይታል። ይህ ድልና ውጤት በESFNA አመራርና በተሳታፊው ኢትዮጵያውያን ብርቱ ጥረትና ቁርጠኝነት የተገኘ እንደሆነ አይጠረጠርም። የአውሮፓው አቻ ማህበርም በተመሳሳይ መልኩ ስልጣን ላይ ባለው መንግስት ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ እጅ የተዘጋጀ እና የተያዘ በመሆኑ በዘንድሮው ዝግጅት ላይ ማንኛውም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ እና ከስርዓቱ ጋር እየተሞዳሞደ የሌለ እውነተኛው የአውሮፓው ዲያስፖራ ወገናችን በሮሙ ፌስቲቫል ላይ እንዳይሰለፍ ተብሎ የተላለፈው መልእክት ፍትሃዊና ተገቢም ሆኖ እናገኘዋለን።

ይህ በሮሙ ፌስቲቫል ላይ ያለመካፈል ውሳኔን በፍትሃዊነቱና በተገቢነቱ ብንቀበለውም ከጊዜያዊ አጭር መፍትሄነቱ አኳያ አንጻር እንጂ ከዘላቂ መፍትሄነቱ አንጻር አይደለምና ምን ይደረግ በሚለው ነጥብ ዙሪያ አመላካች ሀሳቤን ላሰፍር እወዳለሁ።

**ሁለት-የአውሮፓውን ፌስቲቫል ለማስመለስ መደረግ የሚገባቸው ተግባራት

የዘንድሮው 15ኛ የኢትዮጵያውያኑ እስፖርትና ባህል ፌስቲቫል በአውሮፓ ሙሉ በሙሉ በመንግስት ተጠልፎ ተይዟል ግን መመለስና መነጠቅ ይገባዋል ባይ ነኝ። ይህ ማህበር በዲያስፖራ የኢትዮጵያውያኑ  የግል ማህበር እንጂ በመንግስት ተወካይ የኤምባሲ ሰው ቁጥጥር ስር መሆን ያለበት ማህበር አይደለም። ከቶም ቢሆን ሊሆንም አይገባም። የሆነው ሆኖ የቅድሚያ እርምጃው አሁን በሮሙ ፌስቲቫል ላይ ያለመገኘት ተግባር ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ የማህበሩን አመራር መልሶ በመያዝ በውስጡ የተሰገሰጉትን የመንግስት ተወካይ እጆችን ማጥራት ያስፈልጋል።

ይህን ተግባር በሁለት መሰረታዊ ማህበሩን የማጽጃ መንገዶች ማድረግ እንደሚቻልም ለመጠቆም እወዳለሁ።

*1ኛው-መንገድ

አሁኑኑ በመንግስት ቁጥጥር ስር ባለው ማህበር ውስጥ ሆኖ በህጋዊ ምርጫ [ከየእስቴቱ በተወከሉ ተወካዮች የሚሳተፉበት ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ ምርጫ በማካሄድ] ሲሆን።

*2ኛው-መንገድ

በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለውን ማህበር ትቶ ተመሳሳይ አቻ እውነተኛ አዲስ ማህበር በአዲስ ዓርማ  አቋቁሞ ህጋዊነቱን በፍርድ ቤት ከመንግስት ቁጥጥር ስር ካለው መንጠቅ ይቻላል። በእርግጥ እጅግ አጭሩ እና ውጤታማው ከመንግስት እጅ ነጻ የሆነን ማህበር ለማቋቋም ሁለተኛው መንገድ የበለጠ አማራጭ እና ውጤታማ እንደሚሆን ማወቅ ይቻላል።

በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን በየሚኖሩበት እስቴት ከመንግስት አገልጋይነትና አባልነት ነጻ የሆኑ ጠንካራ አስተባባሪ ኮሜቴ ተወካዮችን በመምረጥ በአውሮፓ ደረጃ እንዲሰባሰቡ በማድረግ እስትራቴጂና አካሄድ ፕላን እንዲያወጡ ማድረግ ይገባል። ከየእስቴቱ የተመረጡት ተወካዮች አዲስ ማህበር በማቋቋሙ ወይም የተቋቋመውን መልሶ በመንጠቅ ደረጃ ከአህጉሪቱ ህብረት የማህበራት አደረጃጀትና አመሰራረት ህግ አንጻር የተሻለውን አማራጭ እንዲመርጡ በማድረግ ለተግባራዊነቱ እንቅስቃሴ ማድረግ ይቻላቸዋል።

ይህ እንግዲህ በርቀት እይታ ላይ ሆኖ ሀሳብ ለማቅረብ ለወደደ ሰው አስተያየት የመነጨ ቢሆንም ቅሉ ግን እዚያው አውሮፓ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን የተነጣቃችሁትን ማህበር መልሳችሁ ለመያዝ አስፈላጊነት ላይ የጋራ ስምምነት እንዳለን በማመን የተለያዩ መንገዶችን እና ስልቶችን ከእኔ በተሻለ ቅርብ ያላችሁ ታውቃላችሁ ብዬ አምናለሁና አስተያየቴን ከደጋፊ ሀሳብና እይታ አንጻርም ልታዩት ትችላላችሁ ብዬም አስባለሁ።

የሆነው ሆኖ-በአሜሪካ የኢትዮጵያውያን እስፖርትና ባህል ፌስቲቫል ስኬታማው የሲያትሉ ፌስቲቫል የማህበሩ ነጻ መሆን እና የኢትዮጵያውያኑ አንድነትና ጥንካሬ ውጤት በመሆኑ እናንተም መንግስት ገብቶበታል ብላችሁ ማህበራችሁን በዝምታ እጅ አጣጥፋችሁ በማስረከብ እና ብሎም በማኩረፍ ብቻ እንዳትተውት በጥብቅ ለማሳሰብ ነው ይህን ሀተታ ለመጻፍ የቻልኩት።

ማህበሩ የእናንተ የኢትዮጵያውያን በአውሮፓ ዲያስፖራ ነው። ከምንም መንግስታዊ ተቆጣጣሪነትና ጣልቃ ገብነት የነጻ፣ ነጻ ማህበራችሁ ነው። በምንም ተዓምር ቢሆን ማህበራችሁን እና አገራችሁን ጥላችሁ እንድትሰደዱ ላስገደዳችሁ መንግስት ባላችሁበት ነጻ ሀገር እንዳትተው በጥብቅ ለማስገንዘብ ነው።

በአውሮፓ የኢትዮጵያ መንግስት ሳይሆን ሃያሉ እናንተ ኢትዮጵያውያን መሆናችሁን አትዘንጉ። አውሮፓ ላይ ያለው ስልጣን እናንተ ካላችሁ ዘርፈ ብዙ ስልጣን አንጻር ያነሰ ቢሆን እንጂ አይደለም ሊበልጥ ሊስተካከል እንኳን እንደማይችል ግልጽ ነው። የእናንተ አንድነትና ቁርጠኝነት እጅግ ወሳኝ ነው። በቅርበት እምታውቋቸውን ወሳኝ ተወካዮችን መምረጥ መቻላችሁ ላይ በእርግጠኝነት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባችኋል።

**ሶስተኛ-የሮሙን ፌስቲቫል በተመለከተ

አጠቃላይ ፌስቲቫሉን በሁለት መንገድ መጠቀም ይቻላል፤ ሙሉ በሙሉ ቦይኮት በማድረግ እና ብሎም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊነት መንፈስና ሰንደቅ ዓላማ አጥለቅልቆ የማህበሩን ህገ-ወጠቾን አጋልጦ በስፍራው የተገኘውን ሀገር ወዳድ እና ቅን ኢትዮጵያውያን በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ ለቀጣዩና ዋናው የባለቤትነት መብት ትግል እንዲዘጋጅና እንዲደራጅ ማድረግ ይቻላል። በአጠቃላይ ቦይኮት ያደረጋችሁም ሆነ በፌስቲቫሉ ላይ ለመገኘት የምትችሉ በስፍራው በምታደርጉት የማህበራችሁን መልሳችሁ የመያዝ ጥያቄን እያስተጋባችሁ መሆናችሁን በማወቅ በመካከላችሁ አላስፈላጊ መከፋፈልና ልዩነት እንዳይፈጠር መጠንቀቅ አለባችሁ።

በተለያየ ምክንያት በፌስቲቫሉ ላይ የተገኘ ሁሉ የኤምባሲው አባልና ሰራተኛ ተደርጎ መታየትም ተገቢ አይደለም። ዋናው ቁም ነገርም በፌስቲቫሉ ላይ መሳተፍ እና አለመሳተፍ ብቻ ሳይሆን በፌስቲቫሉ ላይ ተገኝቶ መደረግ የሚገባውን ማድረግና ያለማድረግ የሚወሰን ነው። ማህበራችንን ለማስመለስ በሮሙ ፌስቲቫል ላይ ተገኝተን የባለቤትነት መብታችንን እንገልጻለን፣ ተሳታፊውንም በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ ኢትዮጵያዊነትን እንሰብክበታለን እናደምቅበታለን በሚል ዓላማ የተሰባሰባችሁና የተዘጋጃችሁ ካላችሁ ሀሳባችሁ መልካም ነው ግፉበት። ግን ያለምንም ዓላማና መረዳት የፌስቲቫሉ አድማቂ ሆናችሁ ለመገኘት ያሰባችሁ ባትሄዱ ይመረጣል። ይገባልም!! ከሄዳችሁ ወደሮም በዓላማና በዝግጅት ተነጋግራችሁና ተዘጋጅታችሁበት ይሁን።

ይህን ተግባር መጪውን የ2018 ዓመታዊ በዓል በነጻነት እና በእናንተው ቁጥጥር ስር ባለ ማህበር ለማዘጋጀትና ለማክበር ከወዲሁ መወሰድ በሚገባው እርምጃ ላይ ያተኮረ ጽሁፍ ነው እንጂ የዘንድሮውን የሮሙን ፌስቲቫል በተመለከተ መወሰድ ያለበት እርምጃ ቦይኮት ማድረግ ብቻ እንደሆነ በመግለጽ ጽሁፌን እደመድማለሁ።