ኢትዮጵያውያን በመብራት እጦት እየተሰቃየን መንግስት ለውጭ ሀገራት የመሸጥ ተግባሩን ፍትሃዊ አይደለም ሲሉ አወገዙ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት ላይ የተቀናበረ ልዩ ዘገባ

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያና በአማራው ግዛቶች ውስጥ በከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት ችግር ህብረተሰቡ እየተሰቃየ ባለበት ወቅት መንግስት ለጎረቤት ሃገራት ለጅቡቲና ለኬኒያ መሸጡ አግባብ ያልሆነ ኢ-ፍትሃዊ ተግባር ነው ሲሉ ከአዲስ አበባ ለአባይ ሚዲያ ገለጹ።

ባለፈው ዓመት ተመርቆ ስራ ላይ ከዋለው ግልገል ጊቤ3 በኋላ በኢትዮጵያ ያለው አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ሃይል መጠን ከ4 ሺህ ሜጋዋት በላይ ለአገልግሎት የተዘጋጀ መሆኑን መረጃዎች ቢጠቁሙም ከላይ በተጠቀሱት ግዛቶችና ከተሞች ውስጥ ዛሬም ጭምር ከፍተኛ የሃይል እጥረት በመኖሩ ከሚሰሩበት ቀን ይልቅ የማይሰሩበት ቀን እየበለጠ እንደመጣ ምንጮቻችን ከኢትዮጵያ ይገልጻሉ።

በአጠቃላይ የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል ፍጆታ ከ3 ሺህ 500 ሜጋዋት በላይ ባላለፈበት ሁኔታና የሀገሪቷ አጠቃላይ የሃይል አቅርቦት ከ4 ሺህ ሜጋዋት በላይ በደረሰበት ደረጃ እንኳን ዛሬም ኢትዮጵያውያኑ በመብራት እጦት የሚቸገሩበት ዋና ምክንያት በሃይል እጥረት ምክንያት ሳይሆን በመንግስት ለውጭ ምንዛሪ ሲል ለጎረቤት ሀገራት አሳልፎ በመሸጡ ምክንያት በተፈጠረ እጥረት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ሆኖም የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረቱ በይበልጥ ጎልቶ እሚታየው በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ውስጥ እንዳልሆነ ምንጮቻችን ከኢትዮጵያ ገልጸው በተለይም ትግራይ በጨለማው ከተማረሩት ውስጥ እንዳልሆነችም በአጽንኦት ይገልጻሉ።

በ4.8 ቢሊዮን ዶላር ባጀት በአፍሪካ ትልቁ የተባለለት ባለ 6 ሺህ ሜጋዋት ሃይል ማመንጫ የተባለው የህዳሴ ግድብ ግንባታው በ2017 ይጠናቀቃል በሚል ፕሮግራም መንግስት ከጅቡቲ፣ ክኬኒያ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከታንዛኒያ ጋር የኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ ስምምነት እንዳደረገ የሚታወቅ ሲሆን ግድቡ በ58% የግንባታ ደረጃ ላይ እያለ የሃይል አቅርቦቱ ግን ለኬኒያና ለጅቡቲ መተላለፍ ከጀመረ እንደቆየ ለማወቅ ተችላል።

በኢትዮጵያና ኬኒያ ድንበር ከተማ በሆነችው ሞያሌ የሚኖሩ ነዋሪዎች ከኢትዮጵያ ወደ ኬኒያ የሚላካውን የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያደርሰው ትራንስፎርመር ማሸጋገሪያ በክርተማቸው ሰንጥቆ በማለፍ የኬኒያን ከተሞች እና መንደሮች በብርሃን ሲያደምቅ በትዝብትና በቁጭት እያዩ እንዳለ ከስፍራው ለአባይ ሚዲያ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና በኬኒያ መካከል ከ4 ዓመት በፊት በ69 ቢሊዮን ሽልንግ ኢትዮጵያ በዓመት 400 ሜጋዋት በመጀመሪያ ፌዝ ለመሸጥ እና በሁለተኛው ፌዝ ደግሞ ሽያጩ ወደ 2000 ሜጋዋት እንደሚያድግ ተስማምተው ሲፈራረሙ የአባይ ሚዲያ በስፍራው እንደነበረ ይታወቃል።

እንደ ኬኒያ መብራትና ሃይል ባለስልጣን ጽ/ቤት በኩል Kenya power & lighting Company እና Kenyan Electric Generating Company/KenGen ገለጻ ከሆነ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ በዓመት ልትቀበል ከተስማማችው የኤልክትሪክ ሃይል ግዢ ውስጥ ውስን የሆነውን ክፍል ማግኘት መጀመራቸውን ይገልጻሉ።

በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እና ሕዝብ ብዛት በመያዝ የአንበሳውን ድርሻ ያላቸው ሁለቱ የኦሮሚያና የአማራ ግዛቶች ከትግራይ ጋር ቢነጻጸሩ ማግኘት የሚገባቸውን የሃይል መጠን አቅርቦት ማግኘት ባለመቻላቸው የትግራይ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው 7/24 መስራት የቻሉ መሆናቸውን ጠቅሰው የእነሱ በሃይል አቅርቦት እጥረት ከሚሰሩበት የማይሰሩበት በልጦ መገኘቱ የመንግስትን ዓድሎዓዊ ፖሊሲ የሚገልጽ ነው ሲሉ በምሬት ይናገራሉ።

በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ኢንዱስትሪያቸውን ለማቋቋም በሃይል አቅርቦትና መልካም የቢሮክራሲ አሰራር ባላት ትግራይ ክልል ማቋቋም እንደሚፈልጉ በመግለጽ ትግራይን ሲመርጡ የሚሰማ እውነታ እንደሆነ ይታወቃል።