ታላቁን የጣና ሃይቅ ከእንቦጭ አረም ወረርሽኝ ህልውናውን እንታደግ የሚል ዘመቻ በማህብራዊ ሚዲያ ሲካሄድ ዋለ፤ የጣና ህልውና በአደጋ ላይ መሆኑም ተገለጸ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ህልውናው በአደጋ ላይ ሰለወደቀው የጣና ሃይቅ የተቀናበረ ልዩ-ዘገባ

በክትዮጵያ ውስጥ በግዝፈቱ፣ በታሪካዊ መስህብነቱ እና የቱሪስቶች ቀልብ ሳቢ የሆነው ታላቁ የጣና ሀይቅ በተነሳበት የእንቦጭ ወረርሽኝ አረም ህልውናው በከፍተኛ አደጋ ላይ መውደቁ በገሀድ እያታየ ያለ ቢሆንም የክልሉም ምንግስት እና በተለይም የፌዴራሉ መንግስት ትኩረትን በመነፈጉ ማህበረሰቡ እንዲረባረብ ጥሪ ቀረበ።

“የጣናን ሀይቅ እንታደግ” በሚል መሪ መፈክር ስር ሀገር ወዳድ በሆኑ አክቲቪስት ኢትዮጵያውያን ቅዳሜን ሙሉ ቀን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የንቃተ ግንዛቤ ዘመቻ [Awareness] ላይ እንደተገለጸው ሃይቁ ካለበት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ አኳያ በመንግስት ደረጃ ትኩረትና እውቅና ባለመሰጠቱ ማህበረሰቡ እንዲታደግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን “ከፍተኛ ርብርብና ፈጣን እርምጃን” ከማህበረሰቡ ጠይቀዋል።

ታላቁ የጣና ሀይቅ የአዲስ አበባን ከተማ የቆዳ ስፋት በሚያክል የእንቦጭ አረም ወረርሺኝ እንደተሸፈነ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን አረሙ በእጅግ ከፍተኛ ፍጥነት የሃይቁን ህልውና ጥያቄ ምልክት ውስጥ ባስገባ ደረጃ እየተስፋፋ መሆኑን በስፍራው ጥናት ያደረጉ ጠበብቶች መስክረዋል።

ሀይቁ በወረረው የእንቦጭ አረም የተነሳ በአከባቢው የሚኖሩና ከሃይቁ ዓሳ በማጥመድ ስራ ላይ የተሰማሩ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህልውናም ለአደጋ መጋለጡን በሃይቁ ላይ ጥናት ያደረጉት ሳይንቲስቶች ሪፖርት የገለጸ ሲሆን የአዲስ አበባን ስፋት የሚያክለው እንቦጭ አረም በሃይቁ ውስጥ ያለውን ንጥረ ነገር ተሻሚ በመሆኑ የዓሳ ምርት በከፍተኛ ደረጃ እንዳሽቆለቆለ ተገልጿል።

በሐረር የዓለም ማያ ሃይቅ ከዓመታት በፊት ተመሳሳይ የህልውና አደጋ በተጋፈጠበት ወቅት ከሚመለከተው መንግስታዊ ክፍል እና ብሎም በማህበረሰቡ ትኩረትና የመከላከል እርምጃ ባለመሰጠቱና ባለመወሰዱ ምክንያት ለመድረቅ እንደበቃ አጥኚዎቹ ገልጸው የጣና ሃይቅ አሁን ባለበት ደረጃ ምንም ዓይነት እርምጃ ካልተወሰደ ታሪካዊውና ታላቁ ሃይቅ የዓለም-ማያን እጣ ፈንታ ሲላበስ ለማየት ብዙም ጊዜ የሚፈጅ አይደለም ሲሉ የችግሩን አንገብጋቢነትና አሳሳቢነት የሚገልጹት።

image
በአማራው ክልል መንግስት በኩል ዘግይቶ የተጀመረ ሃይቁን የማዳን ተግባራት ለማየት የተቻለ ቢሆንም ከችግሩ ስፋትና ግዝፈት አንጻር ሲታይ ግን ችግሩ ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ በመሆኑ ይህ ነው የሚያስብል እርምጃ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በጉዳዩ ላይ የቀጥታ ባለጉዳይ እና ሃላፊ የሆነው ማእከላዊው የፌዴራል መንግስት መስጠት የሚገባውን ትኩረት እና ሃይቁን የማዳንን ዘመቻ መሪነትን ሚና እስከ አሁን ሲፈጸምም ሆነ በቅርቡም እንኳን ለመፈጸም የታሰበ ተነሳሽነትም ሆነ ዝግጅት ያለመኖር ጉዳይ ሀገር ወዳድ አክቲቪስቶችን፣ የአከባቢው ተወላጆችና በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎችን በእጅጉ ያሳሳበ ትግባር ሆኖ ተገኝቷል።

image
እንደ ጣና ያለ ታላቅ ሃገራዊ የተፈጥሮ ሃብት በክልሉ መንግስት አቅም ላይ ብቻ መጣል ሕገ-መንግስታዊ መብትና ግዴታ አይደለም የሚሉት ባለሙያዎች የፌዲራሉ መንግስት በቀዳሚነትና በበላይ ሃላፊነት ሃይቁን የማዳን፣ የመከላከልና ብሎም የመንከባከብ ሕገ-መንግስታዊ ግዴታ እንዳለበት ያሰምሩበታል።

በሃይቁ ዙሪያ የሚኖሩና ኑሮዋቸውን በሃይቁ ውሃ ላይ የመስረቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ህልውና ጉዳይ ከሃይቁ እኩል ለአደጋ እንደተጋለጠም መረዳት የተቻለ ሲሆን በአሁን ሰዓት የአካባቢው ነዋሪና ገበሬው ውስን በሆነ አቅማቸው አረሙን ለመመንጠር ሲለፉና ሲጥሩ ተስተውለዋል።

የእንቦጭ አረም-በሃይቁ ውስጥ ያለውን ንጥረ ነገር በመሻማት በሃይቁ ውስጥ ያሉትን እንስሳት እንዳይኖሩ ከማድረጉም በላይ አረሙ ባለው ከፍተኛ ውሃ የመምጠጥና የመጠቀም ባህሪው የሃይቁን የውሃ መጠን በከፍተኛ መጠን እያሳነሰ እንዳለ ከባለሙያዎቹ ጥናት መረዳት ተችሏል።

ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያኑ አክቲቪስቶች የችግሩን አስከፊነትና ግዙፍነት መሰረት በማደረግ ማህበረሰቡ መንግስትና ባለስልጣናቱ ችላ ብለውታል በሚል በዝምታ ከማየት ባላቸው ውስን አቅምና ጉልበት ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ሃይቁን ከጥፋት እንዲታደጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።