አርቲስት ጎሳዬ ተስፋዬ ለአድናቂዎቹና ለወዳጆቹ ከሲያትሉ የኢትዮጵያውያን ፌስቲቫል ላይ መገኘት ያልቻለበትን ሁኔታ በደብዳቤው ገለጸ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋየ=ዬ በዘንድሮው የሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌደሬሽን ተጋብዞ አሜሪካ ቢደርስም በሚቃወሙት ሰዎች አማካኝነት መድረክ ሳይረግጥ ተመልሷል፤ ድምፃዊው ስለሁኔታው የፃፈውን እንሆ፡

“ይድረስ ለኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ የምትገኙ የስራዬ አድናቂዎች በሙሉ ይህን ግልፅ የሆነ መልእክቴን ከአክብሮት ጋር ወደናንተ ይደርስልኝ ዘንድ እወዳለሁ። ኢትዮጵያዊነት ማለት ከአባቶቻችን የወረስነው ጀግንነት፣ ጨዋነት፣ እርስ በእርስ መከባበርና መዋደድ ነውና ዛሬም ከዚህ ማንነት ተካፋይ በመሆኔ የሚሰማኝ ደስታ ወደር የለውም።

ዛሬ ዛሬ እራሳችን በምንፈጥራቸው የሀሳብ ልዩነቶችና ያለመግባባት ችግሮች ሲያጋጥሙን ተወያይተንና ተከባብረን ጉዳዩን በመፍታት ፈንታ ብዙሀኑ ህዝብ በሚጠቀምባቸው ድረገፆች ላይ የተዛባ መልእክቶችን ማስተላለፍ የተለመደ ሆኗል!! እንደሚታወቀው በያዝነው አመት የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌዴሬሽን ላይ ሙዚቃዎቼን ለማቅረብና ከአድናቂዎቼ ጋር ለመገናኘት ዝግጅቴን አጠናቅቄ በስፍራው የተገኘሁ ቢሆንም በጥቂት ግለሰቦች ፍርደገምድል ውሳኔና ጫና እንዳሰብኩት ከአድናቂዎቼ ጋር ሳልገናኝ ቀርቻለሁ።

በዛ ሰአት በተፈጠረው የአድናቂዎቼ መጉላላት ከልብ ባዝንም በሶሻል ሚዲያ ላይ ወጥቼ እሰጥ-አገባ መመላለሱ ስብእናዬና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት አስተዳደጌ ስለማይፈቅድ ብዬ ዝምታን መርጬ የነበረ ቢሆንም፣ እየተላለፈ ያለው የተዛባ መልእክትና የእናንተ የአድናቂዎቼ ፍቅር፣ አክብሮትና የማበረታታት መልእክቶቻችሁ ይህንን እንድፅፍ አስገድዶኛል!! የዚህ አይነቱ የተሳሳተ የስም ማጥፋት ዘመቻ በኔ ላይ ሲፈፀም ኢሄ የመጀመሪያው አይደለም ከዚ በፊትም በሀይማኖት ጉዳይ የተሳሳተ ነገር ተነስቶብኝ የነበረ ቢሆንም በእግዚአብሄር ፈቃድና በእናንተ አድናቂዎቼ ድጋፍ እንደተወጣሁት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው!!

ዛሬም ከእውነት ጎን ቆማችሁ ፍቅራችሁንና ድጋፋችሁን በተለያዩ ድረገፆችና በግል ኢሜል በሜሴንጀር ከጎኔ ቆማችሁ ወገናዊነታችሁን ላደረሳችሁኝ አድናቂዎቼ እና ለእምነታችሁ ያደራችሁ ጋዜጠኞችና ጦማርያን ስለሁሉም ነገር ልባዊ ምስጋናዬ በያላችሁበት ይድረሳችሁ!!!

አሁንም ቢሆን እኔ አርቲስት ጎሳዬ ተስፋዬ ከምንም ነገር የፀዳሁ፣ በኢትዮጵያዊነቴ የማልደራደር፣ እግዚአብሄር በሰጠኝ ፀጋ በሙያዬ ህዝቤንና ሀገሬን እንደማገለግል ቃል እየገባሁ እሰናበታለሁ። እምነት አይሸጥም!!!!” ጎሳዬ ተስፋዬ

በማለት አርቲስቱ ስለሁኔታው በራሱ መንገድ ለአድናቂዎቹና ብሎም ለተቃወሙት ገልጿል