ከአማራና ትግራይ ክልል የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች ባህርዳር ላይ ሽምግልና ተቀምጠው እንደነበር ታወቀ

0

የወልቃይት የማንነት ጥያቄን ለማድበስበስና በትግራይ ክልል እንዲቆይ ለማግባባት ህወሃት መራሹ አገዛዝ 3 ቀን የፈጀ ሽምግልና በባህር ዳር ከተማ ሆም ላንድ ሆቴል ውስጥ እንዳካሄደ ከስፍራው ለትንሳኤ ሬዲዮ የተላከ መልክት አመለከተ።

በሽምግልናው ላይ ቁጥራቸው 300 የሚሆኑ ከትግራይና ከአማራ ክልሎች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች መሳተፋቸውን የገለጸው መረጃ ያለፈው ማክሰኞ ሃምሌ 4 ቀን ሲጠናቀቅ ምንም አይነት መግባባት ላይ እንዳልደረሰ አረጋግጧል። በረከት ስሞኦንና ሌሎች አንጋፋ የህወሃት እና የብአዴን አመራሮች በሽምግልና ስብሰባው ላይ ተሳትፈዋልም ተብሎአል።

የሽምግልና ስብሰባው ያለውጤት የተጠናቀቀበት ምክንያት በተለይ ከትግራይ ክልል የመጡ የአገር ሽማግሌዎች እንደ ህወሃት አመራሮችና ካድሬዎች ሁሉ ወልቃይት በትግላችን መስዋዕትነት የተገኘ ይዞታ ስለሆነ ወደ አማራ ክልል መመለስ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው የሚል የእብሪትና የማስፈራራት አቋም በመያዛቸው እንደሆነ መረጃውን ለዝግጅት ክፍላችን ያደረሱ የሽምግልናው ተካፋይ አረጋግጠዋል።

ከአማራ ክልል ተመልምለው ሽምግልናው ላይ የተሳተፉ የአገር ሽማግሌዎች ወልቃይት የትግራይ ክልል መሆኑን አምነው ከተቀበሉና ህብረተሰቡን ለማግባባት ከቻሉ መንግሥት ለድካማቸው ከፍተኛ የሆነ ገንዘብና ሽልማት እንደሚሰጣቸው በመድረክ ላይ በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደነበረ ምንጮች ገልጸዋል። ህዝብ ሳይወክላቸው በብአዴን አመራሮች ተመልምለው በሽምግልናው ስብሰባ ላይ የተገኙ የአማራ ክልል ሽማግሌዎች ግን መደለያውን አሻፈረኝ በማለት በወገናቸው ኪሳራ የመክበር ፍላጎት እንደሌላቸው አሳይተዋል ።

የሽምግልና ስብሰባውን ለመምራትና ለመታዘብ በስፍራው የነበሩ የኢህአደግ ሃላፊዎች ከሁለቱም ወገን የመጡ ሽማግሌዎች ለየብቻቸው ተመካክረው ልዩነታቸውን እንዲያጠቡ በተደጋጋሚ ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም ሁለቱም በያዙት አቋም በመጽናታቸው ሽምግልናው ያለምንም ውጤት መበተኑ ተገልጿል።

የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት የወልቃይትን ማንነት ለመለወጥ ላለፉት 26 አመታት በርካታ ትግሪኛ ተናጋሪዎችን በስፍራው ካሰፈሩ በኋላ የወልቃይት ህዝብ አማራ ነኝ እንጂ ትግሬ አይደለሁም ብሎ ያነሳውን የማንነት ጥያቄ ለመፍታት ውሳኔ ህዝብ ያካሂድ የሚል አቋም  ጭምር እያንጸባረቁ እንደሆነ ይታወቃል ።