ሌላ ዙር የቤት ፈረሳ ፕሮግራም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተጀመረ፣ ህዝብ ማሰቃየትም የህወሃት አገዛዝ አይነተኛ ባህሪ ነው ሲሉ ተፈናቃዮች ያማርራሉ

0

በዜጎች ስቃይና መከራ ሃብት የማካበት ጥማቱን ለማርካት የሚራወጠው የወያኔ አገዛዝ በኮልፌ ቀራኒዮ ሌላ ዙር የቤት ማፍረስ ፕሮግራም ሰሞኑን እያካሄደ እንደሆነ ታውቋል። በዚህ የቤት ማፍረስ ፕሮግራም በርካታ እናቶች፤ ህጻናትና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ በሠላም ከሚኖሩበት ቤታቸው በሃይል ተገፍተረው ጎዳና ላይ እንዲወድቁ ተደርጓል።

የአዲስ አበባ ከተማ ቦታዎችን እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ በሊዝ በመሸጥ ከፍተኛ ሃብት እያካበተ ያለው የህወሃት አገዛዝ ዜጎችን ከመኖሪያቸው እያፈናቀለ ጎዳና ላይ ለመጣል ለምን የክረምት ወራትን እንደሚጠብቅ የታወቀ ነገር የለም። ሆኖም ግን የህወሃትን ተፈጥሮአዊ ባህሪ ጠንቅቀው የሚያውቁ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚናገሩት፣ በክረምት ቤቶቻቸው የሚፈርስባቸው ሰዎች አገዛዙ የሚፈጽምባቸውን የጭካኔ እርምጃ አደባባይ ወጥቶ ከመቃወም ይልቅ ጎዳና ላይ የሚበተንባቸውን ንብረትና ቤተሰቦቻቸውን ከወቅቱ ዝናብና ብርድ ለመከለል አማራጭ ፍለጋ ላይ ለማተኮር እንደሚገደዱ በመገንዘብ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በኮልፌ ቀራኒዮ በዚህ የክረምት ወቅት እንዲፈርሱ የተወሰነባቸው ቤቶች ከ500 በላይ እንደሆነ ከቤት አፍራሽ ግብረ ሃይል አካባቢ የተገኘ መረጃ ያረጋግጧል። ከነዚህ 500 መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 65ቱ ሰሞኑን ፈርሰዋልም ተብሏል። በላፍቶ፣ ሃና ማሪያም፣ አለም ገናና ሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ የቤት ማፍረስ ዕቅድ በዘንድሮው የክረምት ወራት እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል።

ህወሃት የንግዱን ማህበረሰብ በከፍተኛ የግብር ዕዳ እያንጫጫ በጎን ደግሞ የቤት ማፍረስ እርምጃ እየወሰደ ያለው ባዶ እጁን ያለ ህዝብ ተቃወመ አልተቃወመ የሚያደርስበት ምንም ተጽዕኖ እንደሌለ በማሰብ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።