በአውሮጳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጣሊያን ላይ ሊያካሂዱት ያሰቡት የስፖርት ፌስቲቫል እያወዛገበ ነው

0

በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች በፈረቃ ሲካሄድ የኖረው የእግር ኳስ ጫወታ በዘንድሮው አመት እያወዛገበ መሆኑን በማህበራዊ  ሚዲያዎች ላይ እየተሰራጨ ከሚገኘው ዘገባ ለማረጋገጥ ተችሏል።

በኢትዮጵያዊያን መካከል በየአመቱ የሚካሄደው የእግር ኳስ ጫወታ ዘንድሮ ጣሊያን ዋና ከተማ ሮም ላይ እንደሚካሄድ ተወስኖ በቂ ዝግጅት ከተደረገ ቦኋላ ከህወሃት አገዛዝ ጋር የጥቅም ሠንሠለት በፈጠሩ አንዳንድ አባላት ምክንያት አወዛጋቢ ሆኖ ቦይ ኮት ወይም የተሳትፎ ተዕቅቦ ጥሪ እየተላለፈበት ነው።

የአውሮጳ ኢትዮጵያዊያን ስፖርት ፌደሬሽን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የህወሃት ደጋፊዎችና ጥቅም አሳዳጆች ሰርገው እንዳይገቡና ፌደረሽኑን እንዳያዳክሙት ለመከላከል የህዝብና የወገን ፍቅር ያላቸው የፌደረሽኑ አመራር አባላት ከፍተኛ  ትግል ሲያካሂዱ እንደቆዩ  የሚናገሩ አሉ። በዘንድሮው አመት ሮም ላይ እንዲካሄድ በተደረገው ውድድር ላይ ግን ከቦርድ አባላቱ እውቅናና ፈቃድ ውጪ ዝግጅት ለማካሄድ ሃላፊነት የወሰዱ ግለሰቦች ጣሊያን ከሚገኘው የወያኔ ኤምባሲ ጋር በመመሳጠር መድረኩ የወያኔ መጠቀሚያ እንዲሆን ሰርተዋል ተብሏል።

በዚህም የተነሳ የህወሃት አገዛዝ በህዝባችንና በአገራችን ላይ የሚፈጽመውን ሰቆቃ በማጋለጥ ተግባር ላይ የተጠመዱ አክቲቪስቶች በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሮም በመጓዝ በስፖርት ፈስቲቫሉ ላይ እንዳይሳተፉ ጥሪ ማቅረብ መጀመራቸው ታውቋል።

የህወሃት አገዛዝ ከሼህ አላሙዲን ጋር በመተባበር በሰሜን አሜሪካ የሚካሄደውን የስፖርት ፈስቲቫል ለመጥለፍ ያደረገውን ተደጋጋሚ ሙከራ ኢትዮጵያዊያን አክቲቪስቶች ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ማክሸፋቸው አይዘነጋም። ሰሜን አሜሪካ ላይ ድል ያልቀናው የወያኔ አገዛዝ የአውሮጳን ስፖርት ፌደሬሽን መድረክ ለመጥለፍ ጥረት መጀመሩ ብዙዎችን እያስቆጣ ነው።

በዘንድሮውን የጣሊያ ዝግጅት ላይ ኢትዮጵያዊያን ተአቅቦ አድማ እንዲያደርጉበት ጥሪ እያስተላለፉ ያለው የአክቲቭስቶች ቡድን፤ ህወሃት አገር ውስጥ በወገኖቻችን ላይ እየፈጸመ ያለው ግዲያ ፤ እስርና ዕንግልት እንዲቆም ወገናዊ ሃላፊነት በውጪ አገር የሚያደርገውን ማንኛውንም አይነት እንቅስቃሴ የማስቆም የያንዳንዱ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው ብሎ አንደሚያምን ገልጿል።