ኢትዮጵያውያን በናይሮቢው 88 ሺህ ተመልካች ፊት በ800 እና 1500ሜ የወርቅ ተሸላሚ ሆኑ፣ መሪነቱን ደቡብ አፍሪካ ስትወሰድ ኢትዮጵያ በ4ኛነት ትከተላለች

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በኬኒያ አዘጋጅነት በሚካሄደው የዘንድሮ የአለም አቀፉ አትሌቲክስ [IAAFUnder18] ከ18 በታች ሻምፒዮና ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያን ትናንት ቅዳሜ ከ88 ሺህ በላይ ኬኒያውያን በተገኙበት የካሳራኒ እስታዲየም በ800 ሜትርና በ1500 ሜትር ኬኒያውያኑን አሸንፈው የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆናቸውን አባይ ሚዲያ ከናይሮቢ ዘገበ።

በ800 ሜትርና በ1500 ሜትር አዘጋጇ ኬኒያ የወርቅ ሜዳሊያ እንደምታገኝ የተጠበቀ ሆኖ ሳለ እስታዲየሙን በሞሉት ወገኖቻቸው ፊት ኬኒያውያኑ ብርቱ ፉክክር ያሳዩ ቢሆንም በ800 ሜትር አትሌት መለሰ ንብረት እና አትሌት ቶሎሳ በዳኔ በመጨረሻው ዙር አፈትልከው በመውጣት የአንደኝነትን እና የሁለተኝነትን ደረጃ በመውሰድ ኬኒያውያኑን ኩም አድርገዋል።

በእለቱ በሴቶች 1500 ሜትር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለምለም ሃይሉ 4:20:80 በሆነ ሰዓት በመግባት በእለቱ ለኢትዮጵያ ቡድን ሁለተኛውን ወርቅ ለማግኘት መቻሏን ከናይሮቢ የአባይ ሚዲያ ወኪል ዘግቧል።

ውድድሩ ዛሬ የሚጠናቀቅ ሲሆን እስካሁን በተደረጉት ውድድሮች ደቡብ አፍሪካ በ4 ወርቅ 2 ብር እና 2 የነሀስ ሜዳሊያ በ1ኛነት ደረጃ ስትመራ ኩባ በ4 ወርቅ በ2 ብር እና በ1 ነሀስ በ2ኛነት ደረጃ ስትከተል ቻይና ደግሞ በ4 ወርቅ በ1 ብር እና በ3 ነሀስ የ3ኝነቱን ስፍራ እንደያዙ ታውቋል።

ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በ3 ወርቅ 3 ብር እና በ3 ነሀስ ሜዳሊያ የ4ኛነቱን ስፍራ የያዘች ሲሆን አስተናጋጇ ኬኒያ በ6ኛነት ደረጃ እና ጀማይካ በ5ኛነት ደረጃ ውድድሩን እያካሄዱ እንደለ መረዳት ተችሏል።

image

የዘንድሮው IAAFUnder18 ሻምፒዮን ከሰሃራ በታች ለመጀመሪያ ግዜ በኬኒያ አስተናጋጅነት በናይሮቢ ከሀምሌ 12ቀን 2017 እስከ ሀምሌ16ቀን 2017 እየተካሄደ ያለ አለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ሲሆን ከ139ሀገራት የተውጣጡ ከ2000በላይ አትሌቶች እንደተሳተፉበት ይታወቃል።

image

በአስተናጋጃ ሀገር ተስፋ የተጣለበት የትናንትናው ውድድር ውጤት በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት በመጠናቀቁ ከ80ሺህ በላይ ኬኒያውያን ንዴታቸውን ሲገልጹ በመስተዋሉ ምናልባትም ዛሬ የመዝጊያው ውድድር በተመልካች እጦት እስታዲየሙ ሳይመታ አይቀርም ሲሉ ኮሚንታተሮች ተንብየዋል።