አንተ እያለህ?? [ወንድወሰን ተክሉ]

0

አንተ እያለህ??
አንተ እያለህ
እሱን እሷን ታያለህ
መስለህ ኗሪ እንደሌለህ
አይተህ ሰምተህ እንዳላየህ

እኔን ምንቸገረኝ?
ያለሁ ከጓዳ ከደጅ እማልገኝ

በጎንደር ታች ቆላ
በኦሮሚያ ጋምቤላ
ሲበለቱ በቢላ
አንተ እያየህ በአውላላ

ያልተነካ
የተነካካ
በተመታው እያስካካ
ለገዳዩ በሚያስመካ
በዝምታ አይቶ እየበላ
እየሆነ ለገዳይ ከለላ

ስንቱ አለቀ በሜዳ አውላላ
ሁሉም ለጎረቤቱ ሲላላ
ጎንደር ሲነሳ
እኛነትን እያወሳ
ለነፍሲያው ሳይሳሳ
ዛሬ እንዴት በአንተ ይረሳ?
የኦሮሞን ደም አታፍሰው
የእሱ ጉዳት ጥቃቴ ነው
ይቁም ግድያ
እምትፈጽመውን በኦሮሚያ

ብሎ ለተነሳ
አንተነትህን እያወሳ
ለጠላትህ ሆኖ አበሳ
ዛሬ በአንተ አይረሳ

እንዴት ልይህ
አንተ እንዳለህ
‘መስለህ ስትኖር እንዳላየህ
እንዴት ደፍረህ አለሁ ትለኛለህ?

መስሎሃል የተረፍክ-ያተረፍክ
የእኔነቴን ገመድ አንገትህ ላይ እያጠበክ
አትርፊያለሁ ብለህ ለፈፍክ
ለደመኛህ ሰግደህ ተንበረከክ

የአንተ የእሱ ፈሳሽ ደም
ጎሳ የለሽ አንድ ቀለም
የሰው ልጅ ክቡር ደም
ህልውና ለዚህች ዓለም

ለፍርሃትህ አትሸነፍ
በዝምታ ከቶ አትለፍ
ከገዳዮች አትሰለፍ
ከተጨቋኝ ጎን ተሰለፍ

የአንተ የእሱ ህብረት
የህልውናህ መሰረት
ተከላካይ ከጥቃት
እሚያሸልም ነጻነት

አለሁ በለኝ
በዝምታ ከምታየኝ
ተከተለኝ
ሩቅ ነው ብለህ ሳትርቀኝ

[በጃንዋሪ 2017 ተጻፈ]