በጃዊ እና በቤኒሻንጉል አካባቢዎች ከፍተኛ ውጥረት እንዳለ ተነገረ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
በአሰግድ ታመነ

በመላው ኢትዮጵያ የተቀጣጠለው የነፃነት ትግል አድማሱን እያሰፋ ነው ። የወንበዴው ቡድን ግራ የገባው ሲሆን እንዳበደ ውሻ በመቅበዝበዝ ያገኘውን በማሰርም በመግደልም ትግሉን የሚቀለብሰው መስሎታል።

ለነፃነት የሚደረገው ትግል ከሰሜኑ ክፍል አልፎ በቤኒሻንጉል ክልልም ተስፋፍቷል። ባሳለፍነው ሳምንት ከጃዊ ፈንድቃ ከተማ የ4 ሰዓት በላይ የእግር ጉዞ በኋላ የሚገኘው ከብተሌ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ አቅራቢያ በግምት ከንጋቱ 11፡20 በጥበቃ የአደረ ዋርድያ ጠባቂ ጨምሮ በ2 ወታደሮች ላይ ከየት እንደሆነ ያልታወቀ ጥቃት ተሰንዝሮ ሁሉም መሞታቸው ተሰምቷል።

በቤንሻንጉልና አማራ ድንበር ማንብሉክ በተባለ ስፍራ አካባቢ በታጋዮችና በህወሓት ወታደሮች በጉዞ መንገድ ላይ ድንገተኛ የፊት ለፊት ውጊያውች መካሄዳቸውም ተነግሯል።

የጉዳቱ መጠን በትክክል ባይታወቅም ከሁለቱ ወገን ጉዳቱ ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል።

በቤንሻኒጉል ጠረፋማ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎችን እንዲሁም በእርሻ ስራ የተሰማሩትን ፀረ ሰላም ሀይሎች ገብተዋል በሚል ከፍተኛ አሰሳ እያደረጉ እንደሆነ የአይን እማኞች ተናግረዋል። ከሰሞኑ ትጥቅ ለማስፈታት በሚል ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ጠረፋማ አካባቢዎች የዘመተው የህወሓት/ወያኔ ወታደር በተለዩ ስፍራዎች ከግማሽ በላዩ ሙት ሲሆን ብዙዎች የደረሱበት አይታወቅም። ስርዓቱን ከድተው ወደ ህዝብ የተቀላቀሉም እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።