በኦሮሚያ ከተሞች 3ኛ ቀኑን በዘለቀ አድማ ብዙ ከተሞች ተቀላቀሉ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በምእራብ እና በምእራብ ደቡብ ኦሮሚያ ከሰኞ ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የስራ ማቆም አድማ ለ3ኛ ተጠናክሮ መዋሉን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ይገልጻል።

እረቡእ ሀምሌ 19ቀን ለሶስተኛ ቀን የስራ ማቆም አድማውን የተቀላቀሉት ከጊንጪ ጪሊሞ ደን በኋላ ባሉት የጀልዱ እና የሽኩቴ ከተሞች-በሸኖ፣አርጆ፣ነቀምትና ዙሪያ፣ጉደር ሲሆን ከአዲስ አበባው አስኮ እስከ ሆሎታ በሚወስደው መንገድ ባሉ ከተሞች ውስጥ አድማው እንደቀጠለ ለማወቅ ተችሏል።

የፌዴራሉ ፖሊስ በነቀምት ያልተከፈቱ የንግድ ተቋሞችን ታሽጓል በሚል ወረቀት ሲያሽግ መዋሉን የአይን ምስክሮች የገለጹ ሲሆን በሆሎታ ከንቲባው ነጋዴውን ህብረተሰብ አሰባስቦ “ብትከፍሉ ይሻላችኋል” ብሎ እንዳስፈራራቸው ተናግረዋል።

image
በመንግስት የተመደበው የዘንድሮው የግብር ተመን ከምናስገባው ገቢ እና ወጪ ጋር ተመጣጣኝ ያልሆነና በእጅጉ የተጋነነ ነው በማለት የንግዱ ህብረተሰብ ክፍል እየተቃወመው ሲሆን በመንግስት በኩል ደግሞ ግብር የዜግነት ግዴታ ነው መክፈል ይኖርባቸዋል በሚል አቋም እንደጸና ይታወቃል።
በዚህም መሰረት ቀደም ብሎ የግብሩ ተመኑ ችግር በአዲስ አበባ የተከሰተና የህዝቡንም ተቃውሞ ማስተናገድ የጀመረ ሲሆን ችግሩ በኦሮሚያ፣በአማራው እና በደቡብ ክልሎችም በመከሰቱ አብዛኛው ህዝብ ተቃውሞውን በተለያየ መንገድ እየገለጸ እንዳለ ይታወቃል።