በሰማያዊ ፓርቲ ላይ በባሕርዳር የተከፈተው ክስ በክልል ደረጃ ሊከፈት አይገባም ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ተናገሩ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በዘጠኝ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር እና አባላት ላይ በአማራው ክልል አቃቤ ህግ የተከፈተውን ሕገ-መንግስትን እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓትን በሃይል ለመናድ ተንቀሳቅሳችኋል ክስ በይዘቱ በክልል ደረጃ የማይታይ ከፍተኛ የክህደት/የመፈንቅለ መንግስት/ክስ ነው ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ተናገሩ።

በሳምንቱ መጀመሪያ የአማራ ክልል አቃቤ ህግ በዘጠኙ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር እና አባላት ላይ ነሀሴ 1ቀን 2008ዓ.ም በባህር ዳር በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ወደ ብጥብጥና ሁከት በመለወጥ ለ13 ሰው ህወሃት መጥፋት ለ103ሰው ቀላልና ከባድ መቁሰል አደጋ እና ግምቱ ከ24ሚ ብር በላይ ንብረት መውደም ምክንያት ሆናችኋል ብሎ ክስ መምስረቱን መዘገባችን ይታወሳል።

እንደ አቃቤ ህግ የክስ ይዘት በተጠቀሰው እለት የሰማያዊ ፓርቲ የሰላማዊ ሰልፍ ፍቃድ ጠይቆ እንደተሰጠው የሚገልጽ ቢሆንም የፓርቲው ሊ/ር አቶ የሺዋስ አሰፋ ደግሞ ፓርቲው ፍቃድ ጠይቆ በመከልከሉ ያቀዱትን ሰላማዊ ሰልፍ እንዳላካሄዱ ይናገራሉ።
ሆኖም ፓርቲው ባልጠራበት ሰላማዊ ሰልፍና ህዝቡ እራሱ ተነሳስቶ ባካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ለተፈጠረ ጉዳት ተጠያቂው ጉዳቱን ያደረሰው መንግስታዊው የፖሊስና የወታደር ሃይል መሆኑን አቶ የሺዋስ ገልጸው ፍቃድ የተነፈገው ፓርቲያቸውም ሆነ ህዝቡ ተጠያቂ ሆነው የሚከሰሱበት ምክንያት አይገባኝም ባይ ናቸው።
ሕገ-መንግስቱን እና ሕገ-መንግስታዊውን ስርዓት በሃይልና በጉልበት ለመናድ ተንቀሳቅሳችኋል የሚለው የአቃቤ ህግ ክስ ከፍተኛ ቅጣት [የሞት ፍርድ]የሚያሰጥ መሆኑን የህግ ባለሙያ አቶ ተማም አባ ቡልጉ ለቪ ኦ.ኤ ገልጸው ያንን ድርጊት ለመፈጸም አቅሙና ብቃቱ ያለው መንግስትና መንግስት ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል አቃቤ ህግ ክስ በተራ ቃል ሲገለጽ መፈንቅለ መንግስት የሚል መሆኑን የህግ ባለሙያዎች ተናግረው የክሱ ይዘት በክልል ደረጃ እንኳን የማይታይ ከፍተኛ እና አደገኛ ክስ ነው ሲሉ ይደመጣሉ።
የተለያዩ አመራሩና አባለቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እየታደኑ በመታሰርና በመከሰስ ላይ ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊ/ር አቶ የሺዋስ መንግስት በተለይም የአማራው ክልል መንግስት የፓርቲያቸውን መዋቅር የመነቃቀል ዘመቻ እንደከፈተባቸው ይናገራሉ።