የማዳበሪያ ዋጋ፣ያልተመጣጠነ ግብር ተመን እና የመብራት ሃይል እጥረት የኢትዮጵያውያን ወቅታዊ ፈተና

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ያልተመጣጠነ የግብር ተመን ከነጋዴው እስከ አርሶ አደሩ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ክፉኛ እየደቆሰው መሆኑን ከሰበሰብነው መረጃ ማወቅ ይቻላል።

በአርሶ አደሩ ላይ የተጣለው የግዳጅ ማዳበሪያ ፍጆታም ከምርት ይልቅ እዳን አምጪ ሆኖ በመገኘቱ አርሶ አደሩን ሲያማርር ተሰምቷል። በእነዚህ ወቅታዊ ጉዳዩች ዙሪያ የተጠናቀረው ልዩ ዘገባ እንደሚከተለው ቀርቧል።

የሶስት ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ ሃና ታደሰ በዘመናዊ ልብስ ስፌት ሙያ ከሚተዳደሩት ውስጥ አንዷ ነች። በመርካቶ ባለው ልብስ ስፌት መደብር ከእርሷ ጋር ያሉት በርካታ አጋር ባለሙያዎቻ በቀን ውስጥ ከሚሰሩበት ሰዓት ይልቅ የማይሰሩበት ሰዓት እጅግ ይበልጣል ትላለች። ምክንያቱም የመብራት ሃይል እጥረት በሙሉ አቅማቸው እንዳይሰሩ እንዳደረጋቸው ትገልጻለች። “በዚህን ዓይነት አሰራር ላይ እየተሰቃየን የግብር ተመን ብለው እስትንፋስ አሳጥር ተመን ጫኑብን” በሚል በምሬት ትገልጻለች።

የሃና ታሪክ የአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን የየክልሎቹም ወንድና ሴት ምሬት ታሪክ ነው። በኤሌክትሪክ ሃይል ላይ ጥገኛ የሆኑ አነስተኛ፣ዝቅተኛ እና ከፍተኛም አምራቾችና ሰራተኞች የሃናን ምሬት ይጋራሉ። የውበት ሳሎኖች፣የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪዎች፣ካፍቴሪያና ሬስቶራንቶች፣የጎጆ ኢንዱስትሪዎች ..ወዘተ ከተጣለባቸው ኢ-ፍትሃዊው ግብር ይልቅ የመብራት ፍሰት እንደፍላጎታቸው አለማግኘት ክፉኛ እንደጎዳቸው ይናገራሉ።

“መስራት በምንችለውና መስራትም በሚገባን ሙሉ አቅማችን ሳንሰራ እንዴት አድርገን ነው ይህንን ቁልል የግብር ተመን የምንከፍለው” ሲሉም ግራ በተጋባ ስሜት ይናገራሉ። የመብራት ሃይል እጥረት በራሱ የስራ እና የትርፋማነት እንቅፋት መሆኑ እየታወቀ መንግስት የአቅርቦት ማሻሻል ሳያደርግ ያልተመጣጠነ የግብር ተመን በለፍቶ አደሩ ላይ መጫኑ እስትንፋስን እንደመቁረጥ ነው ባይ ናቸው።

በግብር መክፈሉ ላይ ማንም ያቅማም እንደሌለ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የግብር ተመኑም ቢያንስ በሶስትና በአራት ከፍም ካለ በአምስት እጥፍ ጨምሮ ቢመጣ የምንከፋ አይደለም የሚሉት ግብር ከፋዮች አሁን በመንግስት የተጣለብን ግን የህልውናችንን እስትንፋስ ህቅ የሚያደርግ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዓመታዊ በጀቱ ከ56ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ገልጾ በግብር፣ታክስና ቀረጥ የሚሰበሰበው ግን ከ10ቢሊዮን ብር ብዙም ያልበለጠ ነው በማለት በወጪና ገቢ መካከል ያለውን ከፍተኛ ክፍተት ለማጥበብ የግብር ማሻሻያ ተመን ለመስራት እንደተገደደ ይገልጻል።

የፌዴራሉም መንግስት በመደበው የዘንድሮው ዓመት ከ320ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ ከ57ቢሊዮን ብር በላይ ጉድለት እንዳለው የታወቀ ሲሆን ጉድለቱንም መንግስት ከሀገር ውስጥ አበዳሪ የባንክ ተቋማት በመበደር እንደሚሸፍን ገልጾ ነበር።

ሆኖም በዓመታዊ በጀቱ ውስጥ ከታየው ጉድለት ሌላ በሀገሪታ ውስጥ በተጣለው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ እና በተከሰተው ያለመረጋጋት ምክንያት ያጣው የገቢ መጠን እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ኢኮኖሚስቶች ይናገራሉ። በአንጻሩም በሀገር በቀል ካፒታል ይገነባሉ ተብለው ግንባታ እየተካሄደ ባለው እንደነ የህዳሴው ግድብ ፕሮጄክት መሳይ በርካታ ግዙፍ ሜጋ ፕሮጄክቶችን በውጥን ደረጃ እያካሄደ ያለው መንግስት ከፍተኛ የበጀት ቀውስ እንዳጋጠመው መረዳት ይቻላል።

ይህንንም የካፒታል ፍስትና እጥረትን ለመፍታት እንደመፍትሄ አድርጎ የወሰደው በህብረተሰቡ ላይ ከዚህ በፊት ሲሰበስብ ከነበረው የታክስ፣ቀረጥ፣ግብርና መሰል ክፍያዎችን በመቶኛ እጥፍ አብዝቶ በማቅረብ ማህበረሰቡን ማስጨነቅን ስራዪ ብሎ ተያይዞታል።

በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል ያለው አርሶ አደርም በተመሳሳይ መልኩ በግብር ተመን እና በማዳበሪያ ዋጋ ክፉኛ እያማረረ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። የማዳበሪያ አቅርቦት በህወሃቱ ኤፈርት ድርጅት ሞኖፖሊ ስር ሆኖ የሚከፋፈል ሲሆን የዋጋ ተመኑም በዓለም ገበያ ዋጋ አንጻር ሳይሆን በአምጪው አከፋፋዩ ብቸኛው ኤፈርት ፍላጎትና ተመን እንደሆነ ይታወቃል።

የማዳበሪያ ምርት ለገበሬው የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የግዳጅ ጉዳይ ነው። የማዳበሪያን ምርት ለመጠቀም የመሬቱ ተፈጥሮአዊ ለምነት ያልተነካና ያልተበላ በሆነባቸው ስፍራዎች ሳይቀር ገበሬው ማዳበሪያውን እንዲወስድ ይገደዳል።

በግዳጅ የወሰደውን ማዳበሪያ ደግሞ በዝናብ እጥረት፣በተምች ወረርሽኝና በመሰል ተፈጥሮአዊ ክስተቶች ገበሬው ምርት ቢያጣ አይታለፍም። ልጆቹን ጦም አሳድሮ ጎተራውን አሟጦ፣አራሽ በሬውን ሸጦ ብቻ ተበድሮም ሆነ ተለቅቶ እንዲከፍል ማንቁርቱን ተይዞ ይገዳዳል።
በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣በአማራና በደቡብ ክልል ያሉ ነጋዴዎች የተተመነባቸውን የግብር ተመን ኢ-ፍትሃዊ ሲሉ እየተቃወሙት ነው። በአንዳንድ የምእራብ ኦሮሚያ ግዛቶች ለ3ኛ ቀን በዘለቀ የስራ ማቆም አድማ እያካሄዱ እንደሆነ እየታየ ነው። የትግራይ ክልል ከእነዚህ ሁሉ አሰቃይ ተግባሮች የተነጠለች ይመስል አንዳችም የተቃውሞ ድምጽ ስታሰማ አይሰማም።